መንግስት ከየትኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ነው-- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

486

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ)፦መንግስት ከየትኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 11ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት በ2015 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርት አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ነው።

ኦነግ ሸኔን በሚመለከት ባለፉት ጊዜያት ከአስር ጊዜ በላይ ንግግሮች መደረጉን ገልጸዋል።

“የሰላም ጥሪውን በሚመለከት የኦሮሚያ ክልል የተጀመረ ሳይሆን እንደ ፓርቲ ተነጋግረን ነው የወሰነው፤የሰላም ጥሪው የዚሁ ንግግር ተቀጥያ ነው።” ብለዋል።

ነገር ግን ቡድኑ አንድ የተሰባሰበ ኃይል አለመሆኑ ችግር መፍጠሩን አመልክተዋል።

መንግስት ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንና ይበልጥ የሰው ነፍስ እንዳይጠፋ ለመከላከል የጸጥታ ኃይሉ ጠንካራ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“መንግስት ከየትኛውም ኃይል ጋር ችግሮችን መፍታት የሚፈልገው በውይይትና በንግግር ብቻ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም