የሚዲያ ነፃነትን ያላግባብ በመጠቀም ግጭት ለመቀስቀስ የሚሰሩ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል

276

አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ)፦ የሚዲያ ነፃነትን ያላግባብ በመጠቀም ግጭት ለመቀስቀስ የሚሰሩ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ፡፡

በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ስብሰባ የምክር ቤት አባላት በተለይም በአገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

በትግራይ ክልል ለተፈጠረው ሰላምም የምክር ቤቱ አባላት አድናቆታቸውን ገልጸው፤ መንግሥት የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በኢትዮጵያ አሁን ላይ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ሰላም መኖሩን ተናግረዋል፡፡

 "የዘላቂ ሰላም ግንባታ እንደ ጦርነት ሁሉ በርካታ ጀግኖችን ይፈልጋል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህ ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሰላም ባለቤት በመሆን ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ነገር ግን የግጭት ነጋዴዎች ዛሬም ቢሆን ሆን ብለውና አቅደው ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ለአብነትም አዲስ አበባን የሁከት ማዕከል ለማድረግ በተቀናጀ አግባብ በርካታ ሙከራዎች መደረጋቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህን በማክሸፍ ረገድ የጸጥታ ተቋማት ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተሳካ ሥራ ማከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የሚዲያ ነፃነትን ያላግባብ በመጠቀም ግጭት ለመቀስቀስ የሚሰሩ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸውን ጠቅሰው፤ መንግሥት በመሰል ተቋማት ላይ የሚወስደውን ሕጋዊ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በተለይም አንዳንድ የአገሪቱን መገናኛ ብዙኃን የሟርትና የግጭት ተልዕኮ ይዘው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሚሰበኩትን የግጭትና የጦርነት ቅስቀሳዎች በመተው ለሰላም ትኩረት ሰጥተን እንስራ ሲሉም ተናግረዋል።

"የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ አካላት አሁንም አሉ" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታውን ዘላቂና የተሟላ ለማድረግ በመንግሥት በኩል እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በየትኛውም አካባቢ ሰላም ለማስፈን መንግሥት ሌት ከቀን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ የሰላም ሂደት ዘላቂ የሚሆነው በሥራ በመሆኑ የሁሉም የጋራ ጥረት ሊታከልበት ይገባል ብለዋል።

የዜጎች የመንቀሳቀስ መብት መገደብ እንደሌለበት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለጥፋት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ግን ማስቆም ያስፈልጋል ብለዋል።

በመሆኑም የመንቀሳቀስ መብት ለሰላምና ለልማት ካልሆነ በስተቀር ለጥፋት የሚደረግ እንቅስቃሴ በፍጹም ተቀባይነት የለውም፤ ተጠያቂም ያደርጋል ብለዋል። 

በተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮችን በመፍታት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም