ኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት የሚውል 23 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ-ምድር የውኃ አቅም እንዳላት ተረጋግጧል- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት የሚውል 23 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ-ምድር የውኃ አቅም እንዳላት ተረጋግጧል- የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ መጋቢት 19/2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ለመስኖ ልማት ከ30 ሜትር ባነስ ጥልቀት ላይ የሚገኝ 23 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ-ምድር የውኃ ሃብት እንዳላት መረጋገጡን የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የኢትዮጵያ የውኃ ኃብት አሁን ላይ እስከ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት አቅም ያለው ሲሆን በቀጣይ እስከ 11 ሚሊየን ሄክታር መሬት የማልማት አቅም እንዳለውም ጠቅሷል።
የኢትዮጵያን የአሥር ዓመታት የልማት ግቦች በያዘው መሪ ዕቅድ ውስጥ በኢኮኖሚ ልማት ዘርፍ የግብርናውን መዋቅራዊ ሽግግር ማሳካት ትልቁ ሥራ ሆኖ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ግብርና በዝናብ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ለዝቅተኛ ምርታማነት የተጋለጠ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ የምርት መጠን ከዝናብ መጠን መዋዠቅና በየጊዜው ከሚከሰቱ የድርቅ አደጋዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውጣ ውረዶች ይታዩበታል።
ይህ አካሄድ የሚጠበቀውን የግብርና መዋቅራዊ ሽግግር ለማረጋገጥ ዋነኛ መፍትሔ ባለመሆኑ ለመስኖ ልማት ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑ በዕቅዱ ላይ ተጠቅሷል።
ለዚህም አነስተኛና ትላልቅ ግድቦችን ገንብቶ የሀገሪቱን የገጸ-ምድርና የከርሰ-ምድር የውኃ ኃብት በአግባቡ ለመስኖ ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚሰራም እንዲሁ።
የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ከዝናብ ጠባቂነት የተላቀቀ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ዝናብ ጠብቆ በዓመት አንድ ጊዜ ከማምረት ባሻገር በመስኖ ልማት በዓመት እስከ ሦስት ጊዜ የማምረት እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱንም ጠቅሰዋል።
ለመስኖ ልማት ዕቅድ መሳካት ትልቅ ሚና እየተጫወተ ካለው የገፀ-ምድር ውሃ ባሻገር በሀገሪቱ ከ30 ሜትር ባነሰ ጥልቀት የከርሰ-ምድር የውኃ አቅም መለየቱን ገልጸዋል።
በዚህም በአነስተኛ ጥልቀት ተቆፍሮ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል 23 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ የከርሰ-ምድር ውኃ አቅም መኖሩ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።
ይህን የውኃ አቅም በአግባቡ በማስተዳደር አነስተኛ የመስኖ ልማት ላይ የሚሳተፉ ወጣቶችንና ሴቶች በስፋት ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም ተናግረዋል።
በገፀ-ምድርና አሁን በተረጋገጠው ጥልቅ ያልሆነ የከርሰ-ምድር ውኃ እስከ 6 ሚሊየን ሄክታር ማልማት እንደሚቻል ጠቅሰው፤ በረዥም ጊዜ ውስጥ የውኃ ኃብትን በአግባቡ በመጠቀም እስከ 11 ሚሊየን ሄክታር በመስኖ የማልማት አቅም እንዳለ ተናግረዋል።
በዚህም አሁን በሀገሪቱ ለእርሻ ሥራ ከዋለው 14 ሚሊየን ሄክታር መሬት ውስጥ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን በመስኖ የማልማት ውጥን መኖሩን በመግለጽ።
የገፀ-ምድር ወይም የወንዞችን የተፋሰስ ውኃ ደግሞ ትላልቅ የውኃ መሳቢያ መሰረተ-ልማቶችን በመጠቀም ሰፊ እርሻን እንዲያለሙ እንደሚደረግ ተናግረዋል።