ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በፍትሃዊነት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው-የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ

379

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ) ከህብረተሰቡ ለሚነሱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በፍትሃዊነት አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኣባላት ከመራጭ ኅብረተሰብ የተነሱ ጥያቄዎችን በሚመለከት ከአስፈፃሚ አካላት ጋር ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ የመንገድ፣ የውሃና የመብራት ተደራሽነት ጥያቄዎች  ከኀብረተሰቡ መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡ 

በተለይም ከመብራት እና ከቴሌኮም አገልግሎት መቆራረጥ ጋር በተያያዘ ህብረተሰቡ ምላሽ እንደሚሻም ተመላክቷል።

የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ አለመጠናቀቅ ህብረተሰቡን አሁንም ለቅሬታ የዳረጉ ጉዳዮች መሆናቸው ተነስቷል።

የፕላን እና ልማት ሚንስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ በዚሁ ወቅት መሰረተ ልማትን በፍትሃዊነት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው ጦርነት በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ጉዳት ማድረሱንና ፕሮጀክቶች እንዲጓተቱ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ መንግስት ይህን ለማስተካከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን በማንሳት፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው በመብራት መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች አሁንም ለአገልግሎቱ መቆራረጥ ምክንያት መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

አገልግሎቱ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን የማዘመና የተባላሹ መስመሮች በመጠገን ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩም በአገር አቀፍ ደረጃ የቴሌኮም ኔትወርክ አቅምን የማሳደግ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ኩባንያው የቴሌኮም ተደራሽነትን ለማስፋትና የአገልግሎት ጥራትን ለማረጋገጥ የመሰረተ ልማት ማስፋፋትን ጨምሮ የጥገና ስራዎችን እያከናወነ ስለመሆኑ አብራርተውል፡፡

በበጀት ዓመቱ በአገር አቀፍ ደረጃ 320 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሀመድ አብዱራህማን ናቸው።

ለግንባታ የሚሆኑ ጥሬ እቃዎች ዋጋ መናር አሁንም ዘርፉን እየፈተነው መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን በመቋቋም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም