በጋምቤላ ክልል የውሃና የመሬት ሀብትን ለልማት በማዋል የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየተሰራ ነው--የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ

344

ጋምቤላ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል ያለውን ሰፊ የውሃና የመሬት ሀብት ለልማት በማዋል የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ቢሮ አስታወቀ።

በአርብቶ አደር ፖሊሲና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ላይ የክልሉ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።


 

የቢሮው ኃላፊ አቶ ኮንግ ጆክ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት መንግስት በአርብቶ አደር አካባቢዎች ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ግምት ውስጥ ያስገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ በመቅርጽ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።

የተቀረጸው ፖሊሲ የክልሉን አርሶና አርብቶ አደሮች ኑሮ የሚለውጥና የሚያሻሽል በመሆኑ አመራሩ በቂ ግንዛቤ በማስያዝ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።


 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ፒን ኡጁሉ በበኩላቸው፣ በክልሉ ያለውን ሰፊ የመሬትና የውሃ ሀብት በማልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን ህይወት ለመለወጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የክልሉ አርብቶና አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ በግንባታ ሂደትና ተገንብተው መጠነኛ ችግር ያለበችውን ስምንት የመስኖ ፕሮጀክቶች ወደ ስራ በማስገባት ተጠቀሚ ለማድርግ ስራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ 30ሺህ ሄከታር በላይ መሬት ማልማት የሚያስችሉ 12 ከፍተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል።

ጥናቱ እየተካሄደ ያለው በክልሉ ቢሮ እና በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ትብብር መሆኑን ገልጸዋል

የመስኖ ግብርና ልማቱ ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ሚኒስቴሩ 36 የእርሻ ትራክተሮችን ድጋፍ ማድረጉን ምክትል ቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።


 

በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የቆላማ አካባቢ ምርምር ዴስክ ኃላፊ አቶ አሸብር ደምለው በበኩላቸው መስሪያ ቤቱ ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የአርብቶ አደሩንና ቆላማ አካባቢዎችን የልማት ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተከናወኑት ሥራዎች በቂ ናቸው ባይባልም አበረታች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ሚኒስቴሩ የጀመረውን ድጋፍ የማስተባበር ሥራ አጠናከሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

በቢሮውና በመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ትብብር በተዘጋጀው የአርብቶ አደር ፖሊሲና የማስፈጸሚያ ስትራቴጂ ውይይት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችባለሙያዎች ተሳተፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም