የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለሕዝብ ጥያቄ መፍትሔን የሚያመነጭ አመራርን መፍጠር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

177

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ) የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በመረዳት ለህዝብ ጥያቄ መፍትሔን የሚያመነጭ አመራርን መፍጠር ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። 

በምክር ቤቱ የሰው ሃብት ልማት፣ ሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአካዳሚውን  የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ገምግሟል።

በአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ የእቅድ፣ በጀትና ሪፎርም ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ጫኔ የተቋሙን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።

በዚህም በግማሽ ዓመቱ ማዕከሉ በአዲስ መልክ መቋቋሙን ተከትሎ ተልዕኮውን በማሳካት ረገድ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል።

በተለይም አጫጭር ሥልጠናዎችን መስጠት፣ የውጪ የትምህርት እድሎችን ማመቻቸት፣ የፖሊሲ ምርምሮችን ማካሄድና ተተኪ አመራሮችን ማብቃት ተጠቃሽ ናቸው።

የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመንን ጨምሮ ሥልጠናዎችን በበይነ-መረብ ለማካሄድ የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረጉም እንዲሁ።

ይሁን አንጂ ተቋሙ ከሚጠበቅበት ውጤት አኳያ በቂ ሥራዎች ተሰርተዋል ተብሎ እንደማይታመን አቶ ምትኩ አብራርተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ሪፖርቱን መነሻ በማድረግ ጥያቄና አስተያየት ሰንዝረዋል።

በተለይም ከተቋሙ ስያሜ አኳያ ፓናፍሪካኒዝምን አጉልቶ በማሳየትና ተደራሽነቱን በማስፋት ረገድ ውስንነቶች እንዳሉ አንስተዋል።

በፌዴራል፣ በክልልና የከተማ አስተዳደር አመራሮችን አቅም ከማሳደግ አኳያ ጎልተው የሚታዩ ሥራዎች አለመከናወናቸውንም የቋሚ ኮሚቴው አባላት ገልጸዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በበኩላቸው ማዕከሉ በይፋ ሥራውን ከጀመረ ጊዜ አንስቶ በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑ አይዘነጋም።


 

በተለይም ደግሞ የተቋሙን አሰራር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ያደረገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል። 

የእቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑ ደግሞ በትኩረት ሊታይና ሊፈተሽ እንደሚገባ ሰብሳቢው አንስተዋል።

የሰው ሃይል አቅሙን ማደራጀት፣ የሥልጠና ብቃት ማረጋገጫ ተግባር ላይ መዋሉን ክትትል ማድረግና ወቅታዊና አስቸኳይ የሥልጠና ማንዋሎችን ማዘጋጀትና ተግባራዊ ማድረግ ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል።

በዋናነት የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገነዘብና ለሕዝብ ጥያቄ መፍትሄን የሚያመነጭ አመራርን መፍጠር ላይ አጽንዖት መሰጠት ያስፈልጋል ብለዋል።

የአካዳሚው ፕሬዝዳንት ዶክተር ምህረት ደበበ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ አካዳሚውን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራው ጊዜ የወሰደ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ እቅዱን ማሳካት አልተቻለም ብለዋል።


 

ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በቂ ሥራዎች አለመሰራታቸውን ገልጸው በግማሽ ዓመቱ በሦስት የአፍሪካ አገራት ለሚገኙ የውጭ አገራት ሙያተኞች ሥልጠና ተሰጥቷል ነው ያሉት።

የተልዕኮ መመሳሰል ካለባቸው ተቋማት ጋር በምን መልኩ መሥራት እንደሚያስፈልግ የሚደነግግ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩም አካዳሚው ተልዕኮውን በአግባቡ እንዳይወጣ እንቅፋት ሆኖበታል ብለዋል።   

ያም ሆኖ አሁንም ቋሚ ኮሚቴው የሰጠውን አስተያየት መነሻ በማድረግ አካዳሚው የማስተካከያ ሥራዎችን በመሥራት ለላቀ ውጤት እንደሚተጋ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም