መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል-ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ

269

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ)፦ መንግስት የዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ ገለጹ።

የፍትሕ ስርዓቱን ብልሽቶች ማስተካከል አላማ ያደረገ የሶስት ዓመት የማሻሻያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየካቲት ወር 2015 በምርጫ ክልላቸው በመገኘት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።

የምክር ቤቱ አባላት በውይይቶቹ ከሕብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎችን የያዘ ሪፖርት ዛሬ ለአስፈጻሚ አካላት አቅርበዋል።


 

በሪፖርታቸውም በሁሉም አካባቢዎች በተደረጉ ውይይቶች የሰላም እና ጸጥታ ችግርን ሕብረተሰቡ ማንሳቱን ገልጸዋል።

የዜጎች ተዘዋውሮ የመስራት መብት አለመከበር ጉዳይ መፍትሔ እንዲሰጠው እና የሕግ አስፈጻሚው አካል ሰላምን በሚያደፈርሱ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ አስተማማኝ ሰላምን እንዲያሰፍንም አሳስበዋል።

በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻር ያሉ ብልሹ አሰራሮች እንዲቀረፉ የምክር ቤት አባላቱ የሕዝብን ጥያቄ ዋቢ አድርገው አቅርበዋል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት በመቀስቀስ፣ በመሳተፍና በማስተባበር የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል።

መንግስት በሃይማኖትና በብሔር ሽፋን ግጭት ለመቀስቀስ የሚሞክሩና የአገርን ሰላም የሚያውኩ አካላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የዜጎችን ደህንነት ለማረጋገጥና በሁሉም አካባቢዎች " ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በትኩረት እየሰራ ነው" ብለዋል።

ዶክተር ጌዲዮን አክለውም የፍርድ ቤት ጉዳዮችን ጨምሮ በፍትሕ ተቋማት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የፍትሕ ስርዓቱ ላይ ማሻሻያ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በተለይም አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሙስና ተግባር የሚፈጽሙ አካላት ላይ ቀጣይነት ያለው እርምጃ የመውሰድና ብልሹ አሰራርን የመከላከል ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።

በሌላ በኩል የፍትህ ስርዓቱን ለማዘመን በቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት የሚተገበር የማሻሻያ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታውን ወደስራ ለማስገባት እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸው የፍትሕ ስርዓቱ የሰው ኃይል ብቃት ላይም ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራል ዘላለም መንግስቴ ባለፉት ስድስት ወራት ጠንካራ የሕግ ማስከበር ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት በመቀስቀስ የሰላምና ፀጥታ ችግር የፈጠሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ጠቅሰዋል።

የጸጥታ ስጋቶችን በአግባቡ የመምራት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ መምጣቱን ገልጸው፤ የዜጎችን ሰላምና የሀገርን ልማት የሚያስተጓጉሉ ፀረ-ሰላም ኃይሎች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም