አስፈጻሚ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ የኅብረተሰብ ጥያቄዎች ለመፍታት በትኩረት ሊሰሩ ይገባል - አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

327

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ)፦ አስፈጻሚ አካላት በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ የኅብረተሰብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አሳሰቡ።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመራጭ ኅብረተሰብ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ከአስፈፃሚ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።

ምክር ቤቱ በዓመት ሁለት ጊዜ ከመረጠው ሕዝብ ጋር ውይይት የሚያደርግ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።

ተመራጮቹ በቅርቡ ከመራጩ ሕዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሠላምና ደኅንነት እንዲሁም የኑሮ ውድነትን የተመለከቱ ጥያቄዎች ተነስተዋል፤ እነዚህም ጥያቄዎች ለሚመለከተው አስፈፃሚ አካላት ቀርበዋል።


 

የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሠረት ኃይሌ በየምርጫ ክልሉ በነበረው ውይይት የተነሱ ጉዳዮችን በተመለከተ ሪፖርት አቅርበው ውይይት ተደርጓል።

በዋናነት በውይይቶቹ የሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ቀዳሚ ሲሆን ሌላኛው ከኑሮ ውድነት ጋር የተነሱ ጥያቄዎች አብዛኛውን ድርሻ መያዛቸውን ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነትና ሰው ሰራሽ የምርት እጥረት ኅብረተሰቡን እየፈተነ እንደሚገኝም ተመላክቷል።


 

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚንስትሩ ገብረመስቀል ጫላ የምርት እንቅስቃሴ ላይ ሲስተዋል የነበረው መስተጓጎል አሁን ላይ በተወሰዱ እርምጃዎች ምርቶች በሚፈለገው መጠን መንቀሳቀስ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

እንዲሁም በመላው አገሪቱ ባሉ የእሁድ ገበያዎች ሰፋ ያሉ የግብርና ምርቶች ቀርበው ለኅብረተሰቡ ተደራሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሰው ሰራሽ የዋጋ ንረትና ሕገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እየተወሰደ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ይህንን የኑሮ ውድነት ችግር መቅረፍ በአንድ ተቋም ብቻ የሚፈታ አለመሆኑን የገለጹት ሚንስትሩ ከተለያየ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚተገበር የጋራ እቅድ ተዘጋጅቷል ብለዋል።


 

ከኢኮኖሚ አሻጥሮች ጋር በተየያዘ ችግሮቹ እየተገመገሙ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል።

በቀጣይ መንግሥት ቁጥጥር የሚያደርግባቸው ምርቶች የመለየት ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ አስፈጻሚ አካላት በአጭር ጊዜ መፈታት ያለባቸውን ችግሮች በቅድሚያ መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

እንዲሁም ጊዜ የሚወስዱ ሥራዎች በአግባቡ ለኅብረተሰቡ ማስገንዘብ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አስፈጻሚዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ የኅብረተረሰብ ጥያቄዎችን ለመፍታት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

እንዲሁም የፌደራልና የክልል አመራሮች እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም