የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ከተማው እየገባ ነው-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ከተማው እየገባ ነው-የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከክልሎች ጋር ባደረገው የገበያ ትስስር የግብርና ምርቶች በስፋት ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሚገኙ ተገለጸ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከክልሎች ጋር እያደረገ ባለው የገበያ ትስስር በዛሬው ዕለት ከኦሮሚያ ክልል ከ42 ሺህ ኩንታል በላይ የግብርና ምርት መግባቱ ተገልጿል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አወሉ አብዲ ዛሬ ወደ ከተማዋ ከገቡት የግብርና ምርቶች በተጨማሪ በቅርቡ ከ40 እስከ 50ሺህ ኩንታል ልዩ ልዩ የግብርና ምርቶች በቀጣይ ቀናት ወደ ከተማዋ ይገባሉ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የዋጋ ንረቱን በዘላቂነት ለመቅረፍ ከክልሎች ጋር ባደረገው የገበያ ትስስር የግብርና ምርቶች በሚፈለገው ደረጃና በስፋት ወደ ከተማዋ እየገቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
የግብርና ምርቶችን በመሰወር የገበያ አለመረጋጋት የሚፈጥሩ ነጋዴዎችን ህብረተሰቡ እንዲጠቁም ጥሪ ማቅረባቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።