የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ስርዓትን በማጠናከር በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ደህንነት መጠበቅ ይገባል - የበጎ አድራጎት ማህበራት

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ) የአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ስርዓትን በማጠናከር በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን ደህንነት መጠበቅ እንደሚገባ የበጎ አድራጎት ማህበራት አመለከቱ።

የአዲስ አበባ የሴቶች ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር አድርጓል።


 

የበጎ አድራጎት ማኅበራት ተወካዮች በተለያዩ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ሕጻናት የነገ አገር ተረካቢ በመሆናቸው እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።

በመሆኑም ሕጻናቱን የማሳደግ ሚና የተወሰኑ አካላት፣ የመንግሥትና የድርጅቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ማኅበረሰብ አካላት የጋራ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ብለዋል።


 

በተለይም የአገር ወስጥ ጉዲፈቻን በማጠናከር አቅም ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በጎዳና ላይ ኑሯቸውን ያደረጉ ሕጻናትን ማንሳት እንደሚጠቅባቸው አመልክተዋል።

ለዚህም የግንዛቤ መፍጠር ስራዎች በስፋት ሊሲራ እንደሚገባ ነው የበጎ አድራጎት ማኅበራት ተወካዮች የተናገሩት።


 

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የሴቶችና ወጣቶች መመሪያ ኃላፊ ራምላ ከድር በበኩላቸው  ለችግር የተጋለጡ ሕጻናትን መደገፍ ኃይማኖታዊ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ማህበረሰቡ በተለያየ የችግር ደረጃ ላይ የሚገኙ ሕጻናትን መደገፍና መንከባከብ እንዳለበት ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ የሴቶች ሕጻናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕጻናት መብት ደህንነት ማስጠበቅ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ አናኒያ ያዕቆብ በበኩላቸው በችግር ውስጥ የሚገኙ ሕጻናትን በአገር ውስጥ ጉዲፈቻ ማሳደግ ላይ ያተኮረ የግንዛቤ መፍጠር ስራ እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

በርካታ ሕጻናት በግለሰብ የጉዲፈቻ ስርዓት ውስጥ ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመው የሕጻናቱን ደኅንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ጎን ለጎን እየተከናወኑ ነው ብለዋል።


 

በአዲስ አበባ 2007 እስከ 2014. ባለው ጊዜ ውስጥ 1ሺህ 252 ሕጻናት በግለሰብ ደረጃ በጉዲፈቻ እያደጉ መሆኑን ከከተማው የሴቶች ሕጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ቢሮው በማህበረሰብ አቀፍ የሕጻናት ድጋፍና ክብካቤ፣ መልሶ የማቀላቀልና ከማህበረሰቡ ጋር ማዋሃድ፣ የአደራ ቤተሰብ፣ የአገር ውስጥ ጉዲፈቻና የማሳደጊያ አማራጮችን በመጠቀም ችግር ውስጥ ያሉ ሕጻናትን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም