መንግስት ሁሉም ስፖርቶች ከአበረታች ቅመሞች የፀዱ ሆነው እንዲከናወኑ ጽኑ የሆነ አቋም አለው--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

470

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ)፦መንግስት ሁሉም ስፖርቶች ከአበረታች ቅመሞች ነጻ ሆነው እንዲከናወኑ ጽኑ አቋም እንዳለው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) በበኩሉ ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከኤጀንሲው ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካ ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።


 

አቶ ደመቀ ስፖርት በአገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ከሚጠቅሙ የዲፕሎማሲ መሳሪያዎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የታላላቅ አትሌቶች መገኛ መሆኗን ገልጸው መንግስት ዋዳን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር አበረታች ቅመሞችን ለመዋጋት በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

መንግስት ሁሉም ስፖርቶች ከአበረታች ቅመሞች የፀዱና ነጻ ሆነው እንዲከናወኑ ጽኑ የሆነ አቋም እንዳለውም ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የተቀናጀ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ስርዓትን በመዘርጋት በሁሉም ስፖርቶች አበረታች ቅመሞችን ለመዋጋት እየተከተለቻቸው ያሉ የተለያዩ አማራጮች ውጤታማ መሆናቸውን አቶ ደመቀ አስረድተዋል።


 

የዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) ፕሬዝዳንት ዊቶልድ ባንካ ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ እያከናወነች ያለውን ተግባር አድንቀዋል።

ዋዳ ኢትዮጵያ አበረታች ቅመሞችን ለመዋጋት ያላትን ተቋማዊ አቅም ለመገንባት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዋና መቀመጫውን በካናዳ ሞንትሪያል ያደረገው የዓለም ፀረ-አበረታች ቅመሞች ኤጀንሲ (ዋዳ) የተቋቋመው እ.አ.አ ሕዳር 10/1999 ነው።

ኤጀንሲው በስፖርታዊ ውድድሮች አበረታች ቅመሞች ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የመከታተል፣ የማስተባበርና ግንዛቤ የመፍጠር ስራን ያከናውናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም