የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በትውልዱ ላይ ያሳደረውን የይቻላል መንፈስ በማጠናከር በተባበረ ክንድ  ግንባታውን ማጠናቀቅ እንደሚገባ ተገለጸ

220

ሚዛን አማን መጋቢት18/2015(ኢዜአ)፦ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የይቻላል መንፈስን የፈጠረና ለመጪው ትውልድ የሚተላለፍ ታሪካዊ ቅርስ በመሆኑ ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ቀረበ።   
 
ለግድቡ ግንባታ ገቢ ማሰባሰብን ዓላማ ያደረገ ሁለተኛ ዙር የሕዳሴው ግድብ ጉዞ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ተካሂዷል።
 
ከጋምቤላ ክልል ተነስቶ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለመጣው የጉዞ ልዑክ አባላትም ዛሬ በቤንች ሸኮ ዞን አቀባበል የተደረገ ሲሆን በሚዛን አማን ከተማም ቦንድ የመሸጥ መርሃ ግብር ተጀምሯል።
 
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ አቶ መኮንን መንገሻ እንዳሉት፣ ግድቡ በኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድ፣ ጉልበትና ገንዘብ እየተገነባ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
 
"ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ቢገጥሙም በኢትዮጵያዊያን ህብረት ፈተናዎችን በማለፍ ዛሬ ላይ ደርሷል" ብለዋል።
 
ፕሮጀክቱ የይቻላል መንፈስን የፈጠረና ለመጪው ትውልድ ጭምር የሚተላለፍ ታሪካዊ ቅርስ በመሆኑ ህብረተሰቡ አስከ መጨረሻው ድጋፉን እንዲያጠናክር አቶ መኮንን ጥሪ አቅርበዋል።
 
ተወካዩ እንዳሉት የግድቡ ግንባታ ሥራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት ዓመታት ከ17 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ከኢትዮጵያውያን ተሰባስቧል።
 
ግድቡ ያለ ልዩነት ኢትዮጵያዊያንን ያስተሳሰረ የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው፣ የዛሬው ትውልድ በቀጣይ የሚዘከርበት ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል።
 
አቶ መኮንን እንዳሉት የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ የቦንድ ሽያጭ ሳምንት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ይገኛል።
 
ከቦንድ ግዥ ባለፈ ኢትዮጵያዊያን 8100 ላይ "A" ብለው በመላክ ድጋፋቸውን እንዲያጠናከሩ ጠይቀዋል።
 
የሕዳሴው ግድብ ጉዞ ዋና አስተባባሪ አቶ አምሃ ዓለሙ በበኩላቸው ጉዞው ለግድቡ የሚያስፈልግ ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችል ንቅናቄ የመፍጠር ዓላማ እንዳለውም ተናግረዋል።
 
በዚህኛው ዙር የሕዳሴ ጉዞም 200 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ግብ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል። 
 
በየአካባቢው ከፍተኛ የሕብረተሰብ ተሳትፎ መኖሩን ገልጸው፣ ገቢ የማሰባሰብ ንቅናቄው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ለአንድ ሳምንት እንደሚቆይ ገልጸዋል።
 
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀበሌ መንገሻ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የግድቡ ግንባታ ሥራ ብዙ ጫናዎችን ተሻግሮ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መብቃቱ መላው ኢትዮጵያዊንን የሚያኮራ ነው።
 
የዞኑ ህዝብ ቀሪው የግንባታ ሥራ እንዲጠናቀቅ ቀደም ሲል ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ እንዲያጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም