በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የአይን ሞራ ግርዶሽ የነፃ ህክምና መስጠት ተጀመረ

ሰቆጣ፣ መጋቢት 18 ቀን 2015 (ኢዜአ) በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የአይን ሞራ ግርዶሽና ተያያዥ ችግሮች ላለባቸው አንድ ሺህ ሰዎች ነፃ ህክምና መስጠት መጀመሩን የአስተዳደሩ ጤና መምሪያ አስታወቀ።

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ጤና መምሪያ ምክትል ሃላፊ አቶ አሰፋ ነጋሽ እንዳሉት፤ በዓይን ሞራ ግርዶሽና ትራኮማ ችግር ለአይነ ስውርነት የሚዳረጉ ሰዎችን ለመታደግ የሚያስችል ህክምና ተጀምሯል።


ከዚህ ቀደም ህክምናውን በቅርበት መስጠት ባለመቻሉ ችግሩ ያጋጠማቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ህክምናውን ለማግኘት ደሴና ባህር ዳር ከተሞች ድረስ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።


ችግሩን በቅርበት ለመፍታት ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ የመጡ 10 የሃኪሞች ቡድን የአይን ሞራ ግርዶሽና ተያያዥ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በመለየትና ህክምና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

የሃኪሞች ቡድኑ ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት አንድ ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ህክምናውን እንደሚሰጥ ገልጸው፤ ህክምናው በቅርበት መሰጠት መቻሉ የታካሚዎችን ድካምና ወጪ ማስቀረቱን ተናግረዋል።

ችግሩ ያለባቸውን ወገኖች ልየታ በማድረግ በሰቆጣ ተፈራ ሃይሉ መታሰቢያ ሆስፒታል ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።

የሰቆጣ ከተማ ነዋሪ አቶ መሰረት ምህረቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ የእይታ መጋረድ ችግር እንዳጋጠማቸው ለኢዜአ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት የነፃ የዓይን ህክምና መስጠት መጀመሩ አቅመ ደካሞችን ድካምና እንግልት እንዲሁም የገንዘብ ወጪን የሚያስቀር መሆኑን ገልጸዋል።


አቶ ወንድሙ ታለፈ በበኩላቸው የነፃ የአይን ህክምናው ለበርካታ ዓመታት በዓይን ህመም የሚሰቃዩ ሰዎችን  ተስፋና እፎይታን የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ለሁለት ዓመታት ያክል በዓይኔ ላይ በደረሰብኝ ህመም ምክንያት ለእይታና ለሌሎች ችግሮች አጋልጦኛል ያሉት አቶ ወንድሙ፤ በሚሰጠው ህክምና መፍትሄ እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም