ዘመናዊ የጤና ዘርፍ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ተግባራዊ በማድረግ ለታካሚው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ነው- ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
ዘመናዊ የጤና ዘርፍ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ተግባራዊ በማድረግ ለታካሚው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ነው- ጤና ሚኒስቴር
አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የጤና ዘርፍ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ተግባራዊ በማድረግ ለታካሚው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
"የግሉን የጤና ዘርፍ ተሳትፎ፣ አቅምና ተጠያቂነትን እናጠናክር" በሚል መሪ ቃል አገር አቀፍ የጤና መረጃ ሳምንት እየተከበረ ነው።
የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ተቋሙ በጤናው ሴክተር የሚታየውን የመረጃ ጥራት፣ ተደራሽነት እንዲሁም የአጠቃቀም ጉድለት በማስተካከል ፍትሃዊና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እየተሠራ ነው።
የመረጃ ጥራት በጤናው ዘርፍ የወጡ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ለማሻሻልና ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመቅረጽ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የጤና መረጃ ሥርዓት መዘመኑ በህክምናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ የህክምና ስህተቶችን አጣርቶ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያገኙ ለማድረግና በዘርፉ የሚስተዋሉ የንግድ ማጭበርበሮችን ለመከላከል ይጠቅማል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጄ ዱጉማ።
ጥራቱና ደህንነቱ የተረጋገጥ መድኃኒትን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ እና ተገቢውን የህክምና ምክረ ሃሳብ ለኅብረተሰቡ ለማድረስ የመረጃ አያያዝን ማዘመን አስፈላጊ እንደሆነም አክለዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማት፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች፣ ከግል የጤና ተቋማት ከሌሎችም ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ዘመናዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ሥርዓት በመዘርጋት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የግል የጤና ተቋማት በተለይ በከተማ ደረጃ ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ከሚኒስቴሩ ጋር ጠንካራ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።
ወቅቱን የዋጀ የጤና ዘርፍ የመረጃ አያያዝና አጠቃቀም ተግባራዊ ለማድረግ ከመንግሥት የጤና ተቋማት በተጨማሪ ለግል የጤና ሴክተር የሚደረገው ድጋፍ ይጠናከራል ብለዋል፡፡
የግል ጤና ተቋማት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ በበኩላቸው፤ በጤናው ዘርፍ የመረጃ ሥርዓትን ለማዘመን ከመንግሥትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
የግሉ ዘርፍ የመረጃ ሥርዓት ለማዘመን የሚያስችል በቂ የመሰረተ-ልማትና የሰው ኃይል ያለ በመሆኑ ተቀራርቦ መሥራት ከተቻለ ውጤታማ መሆን ይቻላል ብለዋል፡፡
የጤና መረጃ ሳምንት የጤና ሚኒስቴርን ጨምሮ በተዋረድ እስከ ጤና ተቋማት ድረስ የጤና መረጃ ጥራት ተደራሽነትንና አጠቃቀምን ለማሳደግ ዓላማ ተደርጎ በተለያዩ መርሐ-ግብሮች መከበር ጀምሯል።
በዓሉም ከዛሬ ጀምሮ እስከ መጋቢት 22 በተለያዩ መርሐ-ግብሮች በሁሉም የጤና ተቋማት ይከበራል።