የአረቦን ክፍያ ለማሻሻል የተካሄደው ጥናት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ነው - የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት

186

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ) ከአረቦን (የኢንሹራንስ ዋጋ) ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን በጥናት ለመመለስ የተጀመረው ሥራ እየተገባደደ መሆኑን የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ገለጸ።


የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በሰውና በንብረት ላይ ለደረሰው አደጋ ከ389 ሚሊዮን ብር በላይ የሦስተኛ ወገን መድን የካሣ ክፍያ ፈጽመዋል።

በ2ሺህ 250 ሰዎች ላይ ለደረሰው የሞት፣ የአካል መጉደልና ተመላላሽ ሕክምና ከ41 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ተከፍሏል።

በንብረት ላይ ለደረሰው 10ሺህ 647 አደጋዎች 347 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሦስተኛ ወገን መድን ክፍያ መፈጸሙም ታውቋል።

እነዚህ ክፍያዎች ሙሉ በሙሉ የተሸፈኑት በኢንሹራንስ ኩባንያዎች መሆኑን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ደግሞ ባለፉት ስድስት ወራት አደጋ አድርሰው ባመለጡና የሦስተኛ ወገን ቦሎ ያልለጠፉ ተሽከርካሪዎች በ28 ሰዎች ላይ ለደረሰው የሞትና የአካል ጉዳት ካሣ እንዲሁም ለተመላላሽ ሕክምና ከ900ሺህ ብር በላይ መክፈሉ ተገልጿል።

የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አባሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሦስተኛ ወገን መድን ክፍያ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲቀርብ ትኩረት ተደርጓል።

ለዚህም ደግሞ አሁን ላይ ተቋሙ ከ18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጋር በጋራ በመሥራት ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ አፈጻጸሙ አመርቂ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአረቦን ክፍያ (የኢንሹራንስ ዋጋ) መጠን ለአሥር ዓመታት ባለመሻሻሉ በኢንሹራንስ ኩባንያዎችና ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መሆኑን ገልጸው፤ ይህንን ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያስችል የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው ያስረዱት።  

በተለይም ደግሞ ለተሽከርካሪ ተጎጂ የሕክምና አገልግሎት 2ሺህ ብር እና 40ሺህ ለሕይወት ካሣ የሚቀርበው የአረቦን ክፍያ ከወቅቱ የገንዘብ ግሽበት አንጻር ጥያቄዎች እየተነሱበት መሆኑን አመላክተዋል።

ጎን ለጎንም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በተለይም በንብረትና በሕክምና ካሣ ክፍያ ለኪሣራ ተዳርገናል የሚል ቅሬታ ማቅረባቸውን ነው ያስረዱት።

በሁሉም ወገን የሚቀርቡትን ቅሬታዎች ተከትሎ ተቋሙ በውጭ አማካሪ ድርጅት የአረቦን ክፍያ ማሻሻያ ጥናት ተጠንቶ የማጠቃለያ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።

የሕክምና፣ የሕይወትና የአካል መጉደል ካሣ የአረቦን ክፍያ ጥናት አፈጻጻም 99 በመቶ በመጠናቀቁ በሚያዝያ ወር ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቀርቦ ውሳኔ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል። 

የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከሰቱ የመንገድ ትራፊክ አደጋዎችን የመከላከልና በድኅረ-አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። 

የመንገድ ደኅንነትና መድን ፈንድ አገልግሎት ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ ለ485 ተጎጂዎች የ13 ሚሊዮን ብር የአስቸኳይ ሕክምናና ካሣ እንዲያገኙ አድርጓል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም