በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ለአካታች ዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ እኤአ በ2025 ከ1 ትሪሊየን ዶላር በላይ ገቢ ሊያጡ ይችላሉ- ተመድ

603

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ) በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ትግበራ ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ እኤአ 2025 ከአገር ውስጥ ዓመታዊ ምርታቸው 1 ትሪሊየን ዶላር  በላይ ገቢ ሊያጡ እንደሚችሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ "የፈጠራና ቴክኖሎጂ ለፆታ እኩልነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ውይይት አካሂዷል።


 

የድርጅቱ የሰብአዊ ጉዳዮች የኢትዮጵያ አስተባባሪ ዶክተር ካትሪን ሶዚ፤ የዲጂታል ዘመን ሥራዎችን ቀላል በማድረግ በተለይም ሴቶችና ህፃናትን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል ብለዋል

በዓለም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ከኢንተርኔት ተደራሽነት ውጭ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተደራሽነቱን ማስፋት አስፈላጊ ነው ሲሉ ገልጸዋል

አካታች የዲጂታል ስትራቴጂ ተግባራዊ አለማድረግ በማኅበራዊና የምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፤ አገሮች በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ነው ያሉት። 

አፍሪካን ጨምሮ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ባለፉት አሥርት ዓመታት ለአካታች ኢንተርኔት ትኩረት ባለመስጠታቸው ከዓመታዊ የአገር ውስጥ ምርታቸው 1 ትሪሊየን ዶላር ማጣታቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም መንግሥታት ክፍተቱን ለመሙላት ለአካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትኩረት ሰጥተው ካልሰሩ .. 2025 1 ነጥብ 5 ትሪሊዮን ዶላር ሊያጡ ይችላሉ ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

የክህሎትና እውቀት ክፍተት፣ የኢንተርኔት ዋጋ አቅምን ያገናዘበ አለመሆን፣ ፆታዊ ትንኮሳ፣ የመጠቀሚያ መሳሪያዎች እጥረት የዘርፉ ፈተናዎች መሆናቸውን ዶክተር ካትሪን ገልጸዋል።

2025 ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታዋን የተሳካ ለማድረግ ስትራቴጂ ቀርፃ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ዕቅዱ የተሳካ እንዲሆን አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፉ እየተወሰዱ ያሉ የለውጥ ሥራዎችና የተገኙ ውጤቶችን አብራርተዋል።

2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም የሴቶችን የዲጂታል አቅም ለማሳደግ ክህሎትና እውቀት ላይ ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በሴቶችና በወንዶች መካከል ያለውን የዲጂታል ተጠቃሚነት ዕድልና ክህሎት ልዩነት ለማጥበብ እንደ አገር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በቀጣይም መሰል ተግባራት ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም