የፈጠራና ጥበብ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መቀየር ይገባል - የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር

136

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ)፦ የፈጠራና ጥበብ ኢንዱስትሪ ዘርፍን ወደ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መቀየር እንደሚያስፈልግ የስራ እና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የፈጠራና ጥበብ ኢንዱስትሪ የስራ እድል ማስፋፊያና ግብይት ልማት መፍጠርን አላማ ያደረገ የምክክር መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።

የውይይቱ አላማ ዘርፉን ከማልማት እና ከመደገፍ አንጻር ያሉ እድሎችና ፈተናዎች በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ ማስቀመጥ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የፖሊሲና ስትራቴጂ ጉዳዮች ማናጀር አቶ ልጃለም አዳሙ የፈጠራና የጥበብ ኢንዱስትሪ የዓለምን ስድስት በመቶ ጠቅላላ የምርት መጠን(ጂዲፒ) እንደሚሸፍን ገልጸዋል።

“ዘርፉ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ብዙ የኢኮኖሚ ጥቅም ያለው ቢሆንም እንደ አገር ከዚህ ቀደም እንዲለማ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም” ብለዋል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የፈጠራና የጥበብ ኢንዱስትሪን ለማልማት ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዘርፉን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲሰጥ በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል።


 

“የኪነ-ጥበብ፣ ስነ-ጥበብና ዕደ ጥበብ ፈጠራ ኢንዱስትሪ የስራ ዕድል ማስፋፊያና ግብይት ልማት” እና “የትዕይንታዊ ጥበባት ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ በኢትዮጵያ” በሚሉ ርዕሶች የተዘጋጁ የዳሰሳ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም