ሀገርን የሚገነባ ትውልድ ለማነፅ በጋራ መስራት ይገባናል - ርዕሰ መስተዳድር ርስቱ ይርዳው


ሀዋሳ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ) የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ስብራትን እንደ መማሪያና መስፈንጠሪያ ምዕራፍ በመጠቀም ሀገርን የሚገነባ ትውልድ ለማነፅ ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት ይገባናል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስገነዘቡ።


የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ያዘጋጀው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት ዝቅተኛ የመሆን መንስኤ እና መፍትሔዎች ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ ትላንት በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በወቅቱ እንዳሉት ተማሪዎች የነገ ሀገርን የመገንባት ዕድልና ሀላፊነት አለባቸው፡፡

ተማሪዎች ነገ ሀገርን የሚያሻግሩ ሥራዎችን ለመስራት ከወዲሁ በትጋትና በውጤት መታጀብ እንዳለባቸው አመልክተዋል ።        

የ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤት እንደ ሀገር እጅግ ዝቅተኛ እንደነበር ጠቅሰው "ይህንን የውጤት ስብራት እንደ መስፈንጠሪያ ምዕራፍ በመጠቀም ሀገርን የሚያሻግርና የሚገነባ ትውልድ ለማነፅ በቁጭት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።

"በመሆኑም ውጤታማ ሥራ ለመስራት በጋራ መስራት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው" ሲሉም አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው "በዘርፉ ውጤታማ ስራ ለመስራት በእጃችን ያሉ እድሎችን አሟጠን መጠቀም ያስፈልገናል" ብለዋል።

ለትምህርት ጥራትና ውጤታማነት በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደተጠበቀ ሆኖ የተማሪዎችና የመምህራን ትጋትና ሥነ-ምግባርም ከፍተኛ ድርሻ የሚሰጠው እንደሆነ ተናግረዋል።    

በ2014 የትምህርት ዘመን የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች ባልተመቻ ቸ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው በትጋት በመስራታቸው ያገኙት መሆኑን አመልክተዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ክልል የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዲላሞ ኦቶሬ በበኩላቸው" ለውጤት ውድቀት በዋናነት ሰባት የሚደርሱ መንስኤ የሚሆኑ ጉዳዮች መኖራቸውን በጥናት አረጋግጠናል" ብለዋል።

በየደረጃው ያለው የትምህርት አመራር ኃላፊነቱን በአግባቡ አለመወጣት፣ የመምህራን ሙያዊ ብቃትና ሥነ-ምግባር ከሚጠበቀው በታች መሆን፣ የተማሪው ትጋት ማነስና አላማ ይዞ አለመማርን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ተከታታይ ምዘና አለመኖር፣ በታችኛው ደረጃ ላይ ያለው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዐት ክፍተት፣ የወላጆች ክትትል ማነስ እንዲሁም የትምህርት ቤት አካባቢ ምቹ አለመሆንና ሌሎች ምክንያቶች መሆናቸውን በጥናት መለየታቸውን ጨምረው አመልክተዋል።

በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ፈተና የታየውን እጅግ ዝቅተኛ ውጤት ለመቀየር የተጠቀሱ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ቢሮው በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከመፍትሄዎቹ መካከል የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅትና በቁርጠኝነት መስራት ወሳኝ ሚና እንዳለው አመልክተዋል።

"የንቅናቄ መድረኩ እስከ ታችኞቹ የትምህርት መዋቅሮች እንደሚቀጥል ጠቅሰው የትምህርት አመራሮች፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ ተማሪዎች እንዲሁም ከትምህርት ሥራ ጋር ትሥሥር ያላቸው ሴክተሮች የየራሳቸውን የሀላፊነት ድርሻ ወስደው በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ይደረጋል" ብለዋል።

"ተማሪዎች በግላቸው ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ የሚያስችላቸው ሁኔታ በዙሪያቸው ሊፈጠርላቸው ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል ።

ግብርናን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ሠላምና ፀጥታን በማስፈን የተረጋጋ የትምህርት አሰጣጥ እንዲኖር ማድረግ፣ ትምህርት በጤና መታወክ ምክንያት እንዳይስተጓጎል መከላከል ላይ ያተኮረ የጤና ሥርዐት መዘርጋት ከትምህርት ሥራ ጋር በቀጥታ የሚቆራኙ ተግባራት መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከዚህ አንጻር የሴክተር መስሪያ ቤቶች ቅንጅታዊ አሰራር በተማሪው ውጤት ላይ የሚያመጣው ለውጥ ወደር የሌለው እንደሆነ አስረድተዋል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በ2014 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችና ብዛት ያላቸው ተማሪዎችን ወደ ዩኒቨርሲቲ ላሳለፉ ትምህርት ቤቶች የዕውቅናና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም