ለትንሳኤ በዓል ከ7 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ)፦ ለመጪው የትንሳኤ በዓል 7 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት ለማቅረብ ዝግጅት ማድረጉን የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አስታወቀ።


 

የፊቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር እንያው ዋሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በማህበሩ ስር ያለው የምግብ ዘይት ፋብሪካ የፓልም እና የሱፍ ዘይቶችን ለሃገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል።

ባለፉት ወራትም 100 ሚሊዮን ሊትር በላይ የፓልም ዘይት በማምረት መንግስት በሚያቀርበው ድልድል መሰረት ለተለያዩ ክልሎች ማሰራጨቱን ተናግረዋል።


 

ለመጭው የትንሳኤ በዓልም ህብረተሰቡ ዘይት በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ለማድረግ 3 ሚሊዮን ሊትር በላይ የፓልም እና 4 ሚሊዮን ሊትር በላይ የሱፍ ዘይት ለማቅረብ ከወዲሁ እየተዘጋጀ መሆኑን ኢንጂነር እንያው ገልጸዋል።

የፓልም ዘይቱ በአከፋፋዮች በኩል ለክልሎች እንደሚሰራጭ ጠቅሰዋል።

ፋብሪካው አሁን ላይ 1ሺህ 500 በላይ ለሚሆኑ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ እድል መፍጠሩን ኢንጂነር እንያው አያይዘው ገልጸዋል።


 

በአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የንግድ ውድድር ሸማቾች ጥበቃና መሰረታዊ የንግድ እቃዎች አቅርቦት ክትትል ዳይሬክተር አቶ ታፈረ ይመር እንዳሉት፣ ከጥቂት ወራት በፊት በክልሉ የዘይት አቅርቦት ሰፊ ጉድለት ነበረው።

"መንግስት በዘይት ዋጋ ላይ ያደረገው ድጎማ እንዳለ ሆኖ የፊቤላ ዘይት ወደ ገበያ መግባት የምርት ችግር እንዳይኖርና ዋጋውም እንዲረጋጋ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።

ፋብሪካው ለበርካታ ወጣት ምሩቃን የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጹት ደግሞ በፋብሪካው የሥራ ዕድል ያገኙት ኢንጂነር ትንሳኤ ተስፋ እና ወጣት ስመኝ ክንዴ ናቸው።


 

በኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ የተመረቀውና በፋብሪካው የሰሊጥ ክፍል ማቀነባበሪያ ሃላፊ የሆነው ኢንጂነር ትንሳኤ ተስፋ ከፋብሪካው መቋቋም ጀምሮ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።


 

ወጣት ስመኝም በፋብሪካው ተቀጥራ መስራት ከጀመረች ከሁለት ዓመት በላይ እንደሆናት ጠቅሳ፣ "ፋብሪካው እሷን ጨምሮ ብዙ ወጣቶችን ሥራ በማስያያዝ ከተስፋ መቁረጥ ታድጓል" ብላለች።


 

የፌቤላ ኢንዱስትሪያል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ወደ ሥራ ከገባ ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም