አካታች የዲጂታል ምጣኔ ሀብትን እውን ለማድረግ እውቀትና ክህሎትን ማሳደግ ላይ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካታች የዲጂታል ምጣኔ ሀብትን እውን ለማድረግ እውቀትና ክህሎትን ማሳደግ ላይ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ አካታች የዲጂታል ምጣኔ ሀብትን እውን ለማድረግ እውቀትና ክህሎት ላይ ትኩረት አድርጋ እየሰራች መሆኑ ተገለጸ።
አለም አቀፍ የሴቶች ቀን በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሴቶችን የዲጂታል ተጠቃሚነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት በማድረግ ተከብሯል።
በዚሁ ጊዜ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በኢትዮጵያ በቴሌኮም ዘርፉ እየተወሰዱ ያሉ ሪፎርሞችን አብራርተዋል።
ኢትዮጵያ ተግባራዊ እያደረገች ባለችው ዲጂታል 2025 መርሃ-ግብር ሴቶች ቴክኖሎጂን በሚፈለገው ደረጃ እንዳይጠቀሙ ካደረጉ ችግሮች ውስጥ የዲጂታል ክህሎትና እውቀት ማነስ አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የሴቶችን የዲጂታል አቅም ለማሳደግ ክህሎትና እውቀት ላይ ትኩረት ያደረጉ ተግባራትን በማከናወን አካታች ምጣኔ ሀብትን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሴቶችና በወንዶች መካከል የዲጂታል ዕውቀት ልዩነትን ለማጥበብ እንደ ሀገር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።
በቀጣይ በጥናቱ ግኝት መሰረት እስትራቴጂ በመቅረጽ ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ኢትዮጵያ በዲጂታል 2025 የያዘቻቸውን እቅዶች ለማሳካት ድጋፍ እንደሚያደርግ በመድረኩ ላይ የተገኙት የድርጅቱ ተወካይ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ አካታች ዲጅታል መርሃ ግብሮችን ባለመተግበር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ከኢንተርኔት ተደራሽነት ውጭ እንደሆኑ በመድረኩ ተነግሯል።