ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርናው ዘርፍ በትብብር ለመስራት የተፈራረሙትን የጋራ መግባቢያ  ስምምነት ወደ ትግበራ ለማስገባት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገለጹ


አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና ቻይና በግብርናው ዘርፍ በትብብር ለመስራት የተፈራረሙትን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ወደ ትግበራ ለማስገባት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አስታወቁ።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከቻይና የግብርና ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር ክፍል ዳይሬክተር  ኒ ሆንግሺንግ እንዲሁም በሚኒስቴሩ የዓለም አቀፍ  ትብብር  ክፍል የምዕራብ እስያና አፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር  ሊዩ ጂያንግ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያና ቻይና በግብርናው መስክ በትብብር ለመስራት የፈረሙትን የጋራ መግባቢያ ስምምነት ሊተገበሩ ወደሚችሉ  ፕሮጀክቶች በመቀየር ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ ጠንካራ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።


 

ሁለቱ ወገኖች በግብርና ጉዳዮች ያላቸውን ትብብር አስመልክቶ መደበኛ የሆነ የምክክር ጊዜ ለማዘጋጀት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን በቤጂንግ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያና ቻይና በግንቦት 2014 በግብርና፣ኢንዱስትሪ፣ ፋርማሲዩቲካል፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ መሰረተ ልማትና ጤና መስኮች በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን የኢንቨስትመንት ስምምነቶች መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም