የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የውሃ ሀብትን ከብክነትና ከብክለት በፀዳ መልኩ ለመጠቀም ወሳኝ ሚና አለው--የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር

102

አዳማ መጋቢት 18/2015(ኢዜአ)፦ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት የውሃ ሀብትን ከብክነትና ከብክለት በፀዳ መልኩ ለመጠቀም ወሳኝ ሚና እንዳለው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል

ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ዕቅድ ትግበራ ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአዳማ ከተማ አባገዳ አደራሽ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት ሀብቱን ከብክነትና ከብክለት በፀዳ መልኩ ለመጠቀም ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ሀብቱን ውጤታማ በሆነ መልኩ ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና አገልግሎቶች ለማዋል እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

ለዚህም 10 ዓመት መሪ ዕቅድና የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ተነድፎ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው።

ሰፊ የውሃ ሀብት የሚገኝበትና በሀገሪቷ ከሚገኙ 12 ተፋሰሶች ውስጥ ሰባቱ የሚገኙት በኦሮሚያ ክልል መሆኑን ዶክተር አብረሃ ጠቅሰው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርና አጠቃቀም ስርዓት እውን ማድረግ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በተለይ በክልሉ ያሉ ወንዞችና ሃይቆች ላይ እየደረሰ ያለው ብክነትን፣ ብክለትንና መመናመንን ለመታደግ የተቀናጀ የውሃ ሀብት ስርዓት እውን በማድረግ የውሃ ሀብት በዘላቂነትና በፍትሃዊነት ለመጠቀም ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።


 

ይህንን ማድረግ ካልቻልን የውሃ ሀብቱን ለህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማዋል አንችልም ሲሉም ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም በተፋሰሶች ውስጥ እየተከናወነ ያለው የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት ፍትሃዊ የውሃ ሀብት ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአባይ አዋሽና የስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም የኦሞ፣ ጊቤ ገናሌ፣ ዳዋና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶችን ወደ ተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ስርዓት ለማስገባት በዘርፉ ሙሁራኖች ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ተወካይ ተሻለ በቃና በበኩላቸው የውሃ ሀብት ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል።

በክልሉ የውሃ ብክነትና ብክለት በመቀነስና የውሃ ሀብት ደህንነትን በመጠበቅ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ተቀናጀ የውሃ አስተዳደር ስርዓት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።

የተቀናጀ የከርሰ-ምድርና ገፀ-ምድር የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት በክልሉ ወንዞች ሃይቆችና ተፋሰሶች የውሃ ሀብት ልማቱን ማበልፀግ የጎላ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ ላይ ከኦሮሚያ ሁሉም ዞኖች የዘርፉ ሙያተኞችና ሃላፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም