"በቀጣይ የብልጽግና ፓርቲ ዋናው የቤት ሥራ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀም እና ማስተዳደር ላይ መሥራት ነው"-የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ

296

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ)፦ "በቀጣይ የብልጽግና ፓርቲ ዋናው የቤት ሥራ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀም እና ማስተዳደር ላይ መሥራት ነው" ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

"ድሎችን ማፅናት እና ፈተናዎችን መሻገር" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ወቅታዊ እና ታሪካዊ የአመራር ተልእኮ መድረክ በሀገራዊ የሰላም፣ የፀጥታ እና የልማት ጉዳዮች ላይ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ውይይት አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል።


 

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋናው ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ከተሳታፊ አመራሮች ለተነሡ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ መንግሥታዊ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮችን በሚመለከት ብልጽግና ፓርቲ በትኩረት እንደሚሠራ አበክረው ገልጸዋል።


 

ብልጽግና ፓርቲ አስቀድሞ የጀመራቸውን መርህን መሠረት ያደረጉ ተቋማዊ አሠራሮችን አጠናክሮ በማስቀጠል የፓርቲውን ሕዝባዊ ቅቡልነት ማሳደግ እና ጠንካራ መንግሥታዊ አቅም መፍጠር እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ይህንንም ለማጠናከር አመራሩ የአመለካከት እና የተግባር አንድነቱን በማጠናከር በኅብረ ብሔራዊ አንድነት በተሰናሰለ ወጥ ሀገራዊ እሳቤ አቅም መሆን እንደሚገባው አንሥተዋል።


 

የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካዊ እሳቤዎች ኢትዮጵያዊ መሠረት ያላቸው እና የሀገራችንን እና የሕዝባችንን ችግር ፈቺዎች እንዲሆኑ ማድረግ፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ማሳደግ እና የሕዝቡን ፖለቲካዊ ሞጋችነት እና የልማት ተሳትፎ እንዲሁም ተጠቃሚነት በማሳደግ ቅቡልነትን ማሳገድ እንደሚገባም ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

በአጠቃላይ ብልጽግና ፓርቲ መላ መዋቅራዊ አቅሙን ፈትሾ የሚታዩ የአመራር የአቅም ጉድለቶችን አርሞ፣ ውስጣዊ ብልሽቶችን አክሞ እና መርሕን መሠረት ባደረገ አግባብ ተግባራት በማሳለጥ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ እና ዕድገት በማስቀጠል ሕዝባዊ ቅቡልነትን ማሳደግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር የመጣውን ነፃነት ከመጠቀም ጋር ሰፊ ክፍተት እንዳለ እና ነፃነትን ማክበር እና ማስከበር በሚመለከት ብልጽግና ፓርቲ የሚደራደርበት ጉዳይ እንዳልሆነ አሳስበዋል።


 

እንደመሪ ፓርቲ ነፃነትን በአግባቡ መጠቀምና ማስተዳደር ላይ መሥራት እንደሚገባም አክለው ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ነፃነትን በፓርቲው ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ እና የፓርቲው አመራር እና አባል ተገቢ ነፃነት ተጎናፅፎ ሐሳቡን ያለተፅዕኖ እያራመደ መቀጠል እንዳለበት በአፅንኦት አስቀምጠዋል።

እንደ ሀገር የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ እና የዳኝነት ተቋማት በነፃነት እና በገለልተኝነት ሥራቸውን አጠናክረው መሥራት እንደሚገባቸውም ለተሳታፊ አመራሮች ማንሣታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም