“በዛሬው ጨዋታ ጥሩ ውጤት ይዞ መውጣት የሚያስችል የስነ-ልቦና ዝግጅት አድርገናል”-አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

382

አዲስ አበባ መጋቢት 18/2015 (ኢዜአ)፦ በኮትዲቯር አስተናጋጅነት በሚካሄደው 34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር ሁለተኛውን የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ዛሬ ታደርጋለች።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ በሞሮኮ ራባት በሚገኘውና 45ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ልዑል ሙላይ አብደላ ስታዲየም ከምሽቱ 4 ሰዓት ይካሄዳል።

በምድብ አራት የሚገኙት ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መጋቢት 15 ቀን 2015ዓ.ም ባደረጉት ጨዋታ ጊኒ 2 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የዛሬውን ጨዋታ አስመልክቶ በሰጠው አስተያያት “ከመጀመሪያው ጨዋታ በኋላ አብዛኛው ትኩረት የነበረው ተጫዋቾቹን ከሽንፈቱ በኋላ ከነበረው ስሜት ወጥተው ለዛሬው ጨዋታ በስነ ልቦናና አዕምሮ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ነው” ሲል ገልጿል።

በጊኒ ለተወሰደብን ብልጫ መልስ ለመስጠትና ጨዋታውን ለመቆጣጠር ከአዕምሮ ዝግጁነት ይልቅ አካላዊ ፍልሚያና ስሜታዊነት ላይ ትኩረት ማድረጋችን ለነሱ ይበልጥ እንዲመቻቸው ማድረጉን ተናግሯል።

ይህም ተጫዋቾቹ ከጨዋታው ውጤት ለማግኘት ከነበራቸው ከፍተኛ ጉጉትና በአዕምሯቸው ስለው የገቡትና ሜዳ ላይ የነበረው ነባራዊ እውነት የተለያዩ ከመሆናቸው እንደሚመነጭ አመልክቷል።

“በታዩት ክፍተቶች ላይ ውይይት መደረጉንና ከዛሬው ጨዋታ ጥሩ ውጤት ይዞ ለመውጣት ዝግጅታችንን ጨርሰናል” ነው ያለው አሰልጣኝ ውበቱ።

የአማካይ ተጫዋቹ ጋቶች ፓኖም በሁለት ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት በዛሬው ጨዋታ የማይሰለፍ ሲሆን የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ምኞት ደበበ ከአንድ ጨዋታ ቅጣት መልስ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ መሆኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ የ36 ዓመቱ ቻዳዊ ኢንተርናሽናል ዳኛ አልሀጂ አላው ማህማት በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምድብ አራት ማላዊ ከግብጽ ነገ ከቀኑ 10 ሰዓት በቢንጉ ናሽናል ስታዲየም ይጫወታሉ።

በምድብ አራት ግብጽ እና ጊኒ በተመሳሳይ ስድስት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል።

ኢትዮጵያ በሶስት ነጥብ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች።

ዋልያዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ የመሳተፍ እድላቸውን ለማስፋት የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም