በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች በተከናወነ “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን የማስተዋወቅ እና ሽያጭ መርሐ-ግብር ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ሐረር/ጭሮ/አዳማ መጋቢት 17/2015(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ምዕራብ ሀረርጌ እንዲሁም በምስራቅ ሸዋ ዞኖች በተከናወነ “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን የማስተዋወቅ እና ሽያጭ መርሐ-ግብር ከ157 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ።

በተመሳሳይ በባሌ ዞን መጽሐፉን የማስተዋወቅ እና ከሽያጭ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ ለመፈጸም ቃል ተገብቷል።

 

በምስራቅ ሀረርጌ በተከናወነው መርሃ-ግብር ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የጨፌ ኦሮሚያ አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሰአዳ አብዱረህማን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የተፃፈው “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ለትውልድ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ  ለትውልዱ  እውቀትን ከማሳደግ ባለፈ የቱሪዝም ሃብትን አልምቶ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል። 

በመርሃ ግብሩ ላይ በዞኑ የሚገኙ ባለሃብቶች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ወጣቶችና ሌሎች አካላት ባደረጉት ተሳትፎ ከመፅሃፉ ሽያጭ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ነው ያሉት፡፡

ካሁን ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፉት መፅሃፍት ለትምህርት ቤት እና መሰረተ-ልማት  ግንባታዎች መዋላቸውን አፈ-ጉባኤዋ አስታውሰዋል፡፡

አያይዘውም ከ”መደመር ትውልድ” መፅሃፍ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በክልሉ የሚገኙ እንደ ሶፍ ኡመር ዋሻ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶችን አልምቶ ለመጠቀም እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

የሶፍ ኡመር ዋሻ ታድሶ ለቱሪዝም ክፍት መደረጉ የቱሪዝም ፍሰቱን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግና ቅርሱን ለትውልድ ከማስተላለፍ አንፃር ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡


 

የምስራቅ ሃረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ ሚስኪ መሃመድ በበኩላቸው ከመፅሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ ለአገር መሰረተ-ልማት  ግንባታ የሚውል መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል  ብለዋል፡፡

በየግላቸው የአንድ  አንድ  ሚሊዮን ብር የመፅሃፉን  ግዢ የፈጸሙት ባለሀብቶች ደግሞ  አቶ መሃመድ ሳለህ  እና አቶ ማህዲ አብዱረህማን መፅሃፉ ከትውልድ ግንባታ ባለፈ የቱሪስት ስፍራዎችን ለማልማት የሚውል በመሆኑ በበጎ ተግባር ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

የውጭ ዜጎች ጭምር መፅሐፉን እየገዙት እንደሚገኝ በመጠቆም ለሶፍ ኡመር ዋሻ  የመሰረተ ልማት ግንባታ  የሚውል በመሆኑ ወደ ፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡


 

በተመሳሳይ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን “የመደመር ትውልድ” የተሰኘው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መጸሐፍን ለማስተዋወቅ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር 25 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የዞኑ አስተደዳር ገልጿል፡፡


 

በዛሬው እለት በተካሄደው “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ የማስተዋወቅ ስነ-ስርዓት ላይ ከባለሀብቶች፣ ከዞኑ፣ ከወረዳዎችና ከከተማ አስተዳደሮች 25 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን የዞኑ አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጣሃ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በምስራቅ ሸዋ ዞን በተከናወነ “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍ ማስተዋወቅና ሽያጭ መርሃ-ግብር ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል።


 

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ እንደገለፁት “የመደመር ትውልድ” መጽሐፍን ለዞኑ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ በተካሄደው ፕሮግራም ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ መከናወኑን ተናግረዋል።

በመፅሃፉ ማስተዋወቅ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የኦሮሚያ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ ”የመደመር ትውልድ” መጸሐፍ ስለ መጪው ትውልድና በመጪው ጊዜያችን ምን መስራት እንደሚገባን በግልጽ ያስቀመጠ ነው” ብለዋል።

ለአሁኑና ለነገ ትውልድ የተሻለ ተስፋን ያመላከተ ነው ያሉት ሃላፊዋ ከመጸሐፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ የክልሉን ታሪካዊ ቦታና የቱሪዝም ሀብቱን ለማልማት ትልቅ ሚና ያለው ነው ብለዋል።


 

በዚህም የሶፍ ዑመር ዋሻን ጨምሮ ታሪካዊ ቦታዎች ለምተው ለቱሪዝም ዕድገቱ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ ከማስቻሉም ባለፈ ለትውልድ እንዲተላለፉ የሚያስችል አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የዞኑ ነዋሪዎች  መፅሐፍን በመግዛት የልማት አጋርነታቸውን በተግባር በማረጋጣቸው አመስግነዋል።

በተመሳሳይ "የመደመር ትውልድ” (Dhaloota Ida'amuu) መጸሐፍ በባሌ ዞን ደረጃ የማስተዋወቅና ሽያጭ መርሃ-ግብር የተካሄደ ሲሆን ነዋሪዎች እና ባለሀብቶች ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ግዢ ለመፈጸም ቃል ገብተዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ ባስተላለፉት መልዕክት፣ መጸሐፉ ትውልድ ትክክለኛውን ታሪክ እንዲረዳ ከማድረግ በተጓዳኝ በሽያጩ የሚገኛው ገቢ ለልማት ወዋሉ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም