በምሥራቅ ባሌ ዞን የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ ታሳቢ ያደረገ 155ሺህ ሄክታር መሬትን የሸፈነ የተፋሰስ ልማት ስራ መሰራቱ ተገለጸ

711

መጋቢት 17/2015 (ኢዜአ) በምሥራቅ ባሌ ዞን የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ ታሳቢ ያደረገ 155 ሺህ ሄክታር መሬትን የሸፈነ የተፋሰስ ልማት ስራ መሰራቱን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለጸ።

በዞኑ ባለፉት ሁለት ወራት ሲካሄድ የነበረው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራ መጠናቀቁን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት እንደገለጸው ባለፉት ሁለት ወራት በተከናወነው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ስራ 155ሺህ ሄክታር መሬት የሸፈነ የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል።

የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከድር ይሳቅ በተቀናጀ የአፈርና ውኃ ጥበቃ የተከናወኑ ሥራዎች የድርቅ ተጋላጭነትን በመቀነስ በኩል ጉልህ አስታዋጽኦ እያበረከቱ ነው። 

በዞኑ ስምንት ወረዳዎች ከ155ሺህ ሄክታር መሬትን በመሸፈን በተከናወነው በዚህ ሥራ 3ሺህ ሄክታር መሬትን ከእንስሳት ንክኪ ማካለልን ጨምሮ የችግኝ ዝግጅት፣ 20ሺህ ኪሎ ሜትር የማሳና የተራራ ላይ እርከን ስራ፣ የግጦሽ መሬት ልማትና ሌሎች የድርቅ ተጋላጭነትን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

አቶ ከድር እንዳሉት፣ በዞኑ በተደጋጋሚ እየተሰሩ የሚገኙ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የድርቅ ተጋላጭነትን ከመቀነስ በተጓዳኝ የሥራ ዕድል ምንጭ እንዲሆኑ ከ4ሺህ የሚበልጡ ወጣቶችን በዘርፉ ማደራጀት ተጀምሯል።

በዞኑ የዳዌ ቃቸን ወረዳ የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ አሚን እንዳሉት፣ በአካባቢያቸው በተደጋጋሚ እያጋጠመ የሚገኘውን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ ለተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ትኩረት ተሰጥቷል። 

በወረዳው የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ የተከናወነባቸው ተፋሰሶች በዘላቂነት እንዲጠበቁ ከ30 የሚበልጡ ወጣቶችን በተፈጥሮ ኃብት ማህበራት እንዲደራጁ ተደርጓል ብለዋል። 

ወጣቶቹ ከእንስሳት ንክኪ በተከለሉና በተፈጥሮ ኃብት በተሸፈኑ አካባቢዎች ውስጥ የንብ ማነብ፣ የእንስሳት መኖ ልማት፣ ሌሎች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችን እንደሚያከናውኑ ነው የገለጹት።

በዳዌ ቃቸን ወረዳ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከተሳተፉ ነዋሪዎች መካከል አቶ ያህያ አብዱልወሃብ በሰጡት አስተያየት፣ የተቀናጀ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራዎች የድርቅ ተጋላጭነትን እንደሚቀንሱ በማመን በስራው መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በተለይ ዘንድሮ በአካባቢያቸው በተከናወኑ ሥራዎች ላይ ወጣቶች እንዲደራጁ መደረጉ ሥራውን ውጤታማ ያደርገዋል ነው ያሉት። 

ወጣት ሙክታር መሐመድ በበኩሉ፣ በሰው ሰራሽ ተጽእኖ የተነሳ አካባቢያቸው ተራቁቶ እንደልብ ይፈሱ የነበሩ ወንዞች በመድረቃቸው ለድርቅ መጋለጣቸውን አስታውሰዋል። 

ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች የተራቆተው አካባቢ አረንጓዴ እየለበሰ መምጣቱ ተስፋ እየሰጣቸው መሆኑን ነው የገለጹት። 

በአሁኑ ወቅት ከሌሎች 15 የአካባቢያቸው ወጣቶች ጋር የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ማህበራት በመደራጀት በንብ ማነብና የእንስሳት መኖ እየተሳተፈ መሆኑን አመልክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም