የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየተሰራ ነው - የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚደንት አወሉ አብዲ

አዳማ መጋቢት 17/2015 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚደንት አወሉ አብዲ ገለጹ።

በክልሉ በመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቀነስና በአገልግሎት ማሻሻል ላይ በተሰሩ ስራዎች 40ሺህ በሚጠጉ አመራሮችና ሙያተኞች ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አወሉ አብዲ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት የክልሉ መንግሥት የተገልጋዩን ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታትና ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ በትኩረት እየሰራ ነው።

በተለይም ባለፉት ሰባት ወራት የመልካም አስተዳደር ችግር የሚስተዋልባቸውን ተቋማት ለመለየት በክልሉ ፕሬዚደንት የቅርብ ክትትል የሚደረግበት ልዩ ግብረ-ሃይል በማደራጀት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ በምክትል ፕሬዚደንት የሚመሩ ልዩ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን አቶ አወሉ አብዲ ገልጸዋል።

ኮሚቴውም የመጀመሪያ ስራው ችግሮችን መለየት ላይ ትኩረት አድርጎ በመሰራቱ በክልሉ መስሪያ ቤቶች ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም በሁሉም መስሪያ ቤቶች ላይ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች መኖራቸውን በማረጋገጥ ወደ መፍትሄ ዕቅድ ዝግጅት መገባቱን ተናግረዋል።

የመንግስት ስራ ሰዓት ካለማክበር ጀምሮ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት አቶ አወሉ ''አብዛኛው ሰራተኛ አራት ሰዓት ቢሮ ገብቶ ዘጠኝ ሰዓት እንደሚወጣ በተለያየ ጊዜ ከተገልጋዮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች ማረጋገጥ ተችሏል'' ብለዋል።

በዚህም አገልግሎት ፈላጊው ህዝብ ከመጉላላት ባለፈ 'እጅ መንሻ' ጭምር እየተጠየቀ መሆኑን መረዳት እንደተቻለ ተናግረዋል።

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገለፃ አንዳንድ አመራሮችም ስብሰባዎችን ጨምሮ የኮሚቴና ሌሎች ጉዳዮችን ሽፋን በማድረግ የመልካም አስተዳደር ችግር እየፈጠሩ መሆናቸው መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ችግሮቹ ከተለዩ በኋላም በየመስሪያ ቤቱ መፍትሄ ማምጣት የሚያስችሉ ሪፎርሞች እንዲካሄድ በመደረጉ የተወሰኑ ለውጦች ታይተዋል ብለዋል።

በተለዩት ችግሮች መነሻ በማድረግ ችገሮቹን ለመቀነስና የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል 40ሺህ በሚጠጉ አመራሮችና ሙያተኞች ላይ የተለያየ እርምጃ ተወስዷል ብለዋል።

እርምጃ የተወሰደባቸው አመራሮችና ሰራተኞች በሙስናና 'እጅ ማንሻ' በመጠየቅ፣ ሌብነትና ብልሹ አሰራር ውስጥ በመሳተፍ መረጃ የተገኘባቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የተወሰደው እርምጃም ከቃል ማስጠንቀቂያ ጀምሮ ከቦታ ማንሳት፣ ከደረጃና ከደመወዝ ዝቅ ማድረግ፣ ከስራ ማሰናበትና በህግ ተጠያቂ ማድረግ ጭምር የሚያካትት መሆኑንም አስረድተዋል።

እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን በክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥን የማዘመን ስራዎች በስፋት እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዚህም ንግድ፣ መሬት፣ ማዘጋጃ ቤት፣ ፍርድ ቤቶችን ጨምሮ የህዝቡ የዕለት ተዕለት አገልግሎት የሚበዛባቸው ተቋማት ላይ አገልግሎቱን ወደ 'ዲጂታል' የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከመዝገብ ቤት ጀምሮ ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ለመለወጥና ከሰው ንክኪ ነፃ ለማድረግ የቴክኖሎጂና ዲጂታላይዜሽን አገልግሎት መጀመራቸውን አክለዋል።

በተጨማሪም እያንዳንዱ አመራር በሳምንት ሶስት ቀን ቀኑን ሙሉ ቢሮ ሆኖ ህዝቡን እንዲያገለግል የክልሉ መንግስት ወስኖ ወደ ተግባር መግባቱን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ በክልል ደረጃ በምክትል ፕሬዝዳንቱ የሚመራ የተለያየ ኮሚቴ ተደራጅቶ ክትትልና ቁጥጥር በማድረጉ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከወረዳ ጀምሮ በከተሞችና በዞኖች መሻሻሎች መኖራቸውን አመልክተዋል።

ይሁንና ችግሮቹን በመሰረታዊነት ለመቅረፍ ሪፎርምና ማሻገር ላይ በቀጣይ ስራ የሚፈልጉ ጉዳዮች መሆናቸውን አቶ አወሉ አብዲ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም