ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በዶሮ እርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ መጋቢት 17/2015(ኢዜአ) የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር በዶሮ እርባታ ዘርፍ ለተሰማሩ ወጣቶች ትልቅ ዕድል ይዞ መምጣቱን ኢዜአ ያነጋገራቸው ዶሮ አርቢዎች ገለጹ።

የግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ ኢትዮጵያ ከዶሮ ስጋ እና እንቁላል ከፍተኛ ጥቅም እንድታገኝ እየሰራ መሆኑን ገልጿል።


 

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ ነዋሪው ወጣት ማንደፍሮ ሽፈራው፤ ከሁለት ዓመት በፊት ከጓደኞቹ ጋር የሕብረት ስራ ሽርክና ማኅበር መስረተው የጀመሩት ዶሮ እርባታ ጥሪት ማፍራት እንዳስቻላቸው ይናገራል።


 

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሀን ከተማ ነዋሪዋ ሠላም ታደሰም ከሰባት ዓመት በፊት ከዩኒቨርሲቲ ተመርቃ ስራ በማጣቷ፤ ከመሰል ጓደኞቿ ጋር 15ሺህ ብር ብድር በዶሮ እርባታ ሽርክና ማህበር ተደራጅተው ስራ መጀመራቸውን ትገልጻለች።

ሰላምና ጓደኞቿ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ከመለወጥ አልፈው አሁን ላይ ለሌሎች ሴቶች የስራ እድል መፍጠር ችለዋል።


 

እንደ ማንደፍሮ እና ሰላም ሁሉ በዶሮ እርባታ የተሰማሩት ወጣት ሰላም ደምሴ እና ወጣት ብሩክ ግርማ ዶሮ እርባታ በቀላሉ የሚከወን፣ በቶሎ ወደ ትርፍ የሚወስድ ዘርፍ መሆኑን ይገልጻሉ።

ወጣቶቹ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከወራት በፊት ያስጀመሩት ሀገር አቀፍ የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር፤ የዶሮ እርባታ ዘርፍ ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ማድረጉን ተናግረዋል።


 

መንግስት በሌማት ትሩፋት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በገበያ ላይ ካለው የዶሮ እና እንቁላል ምርት ተፈላጊነት መጨመር ጋር ተዳምሮ ለዶሮ አርቢዎች ትልቅ እድል ፈጥሯል ነው ያሉት።

በቀጣይ ኢንቨስትመንታቸውን በማስፋት የስጋ ዶሮና እንቁላል ከማቅረብ በተጨማሪ የዶሮ ስጋን እሴት ጨምሮ ለገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳላቸው ገልጸዋል።  

በገበያው ላይ ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ዶሮ አርቢዎች በጫጩት አስፈልፋይ ድርጅቶች ላይ ሰፊ ወረፋ እንዲጠብቁ እያደረጋቸው መሆኑን አንስተዋል።


 

የዶሮ ጫጩት እና የዶሮ መኖ ዋጋ መናር እንዲሁም የፋይናንስ አቅርቦት ክፍተትም ሌላው ተግዳሮት በመሆኑ መንግስት መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ አንስተዋል።

የዶሮ ስጋ በአንጻራዊነት የዋጋ ቅናሽ ያለው መሆኑን በመግለጽ ይህም ህብረተሰቡ የዶሮ ስጋን በአማራጭ ምግብነት እንዲጠቀም እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወጣቶች በዶሮ እርባታ፣ በእንቁላልና ተያያዥ ዘርፎች ላይ ቢሰማሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው ያነሱት።


 

በግብርና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ካሳው አምሳሉ፤ በእንስሳት ሀብት ልማት እምቅ አቅም ባላት ኢትዮጵያ፤ የሌማት ትሩፋት ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን አምጥቷል ብለዋል።

ከነዚህም መካከል ዶሮ እርባታ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ዶሮ አርቢዎች በዕውቀትና በክህሎት ተደግፈው እንዲያረቡ ለማድረግና የዶሮ ምርታማነትን ለመጨመር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የዶሮ እርባታ ዘርፍ በቀላሉ ሊሰራ የሚችልና ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በተለይ፤ በስነ ምግብ የበለጸገ ትውልድ ለመገንባት ትልቅ አቅም እንደሆነ ገልጸዋል። 

የሌማት ትሩፋት መርሐ-ግብር ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ወዲህ ዘርፉ መነቃቃት ማሳየቱን ገልጸው፤ ከፍላጎት ማደግና ከጫጩት አቅርቦት አንጻር ክፍተት መኖሩን ጠቁመዋል።


 

በዚህም መንግስት በጫጩት አስፈልፋይነት የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶችን ቁጥር ለመጨመር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ የጫጩት አቅርቦት ከገበያው ፍላጎት ጋር  እንዲጣጣም ይሰራል ነው ያሉት። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለአራት ዓመታት የሚተገበር ብሔራዊ የሌማት ትሩፋትመርሐ-ግብርን ጥቅምት 23 ቀን 2015. በአርባ ምንጭ ከተማ በይፋ ማስጀመራቸው ይታወቃል።

'የሌማት ትሩፋት' መር-ግብር በምግብ ሉዓላዊነት ማስከበር እና ክብርን ማስጠበቅን ያለመ ሲሆን በተለይም ስጋ፣ እንቁላል፣ ማር እና ወተት ቅንጦት ሳይሆን ትርፍ ምርት ሆነው እንዲገኙ ማስቻልን ግብ አድርጓል።

ለቀጣይ አራት ዓመታት በሚተገበረው በዚህ መርሀ-ግብር የዶሮ ስጋ ዓመታዊ ምርትን አሁን ካላበት 90ሺህ ወደ 240ሺህ ቶን ለማሳደግ ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም