የህዳሴ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ መጠናከር አለበት - ዶክተር አረጋዊ በርሄ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድቡ በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ መጠናከር አለበት - ዶክተር አረጋዊ በርሄ
አሶሳ፣ መጋቢት 16 /2015 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ ለመከላከል የሚያስችል የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ መጠናከር አለበት ሲሉ የግድቡ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ አስገነዘቡ።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ ሃገር አቀፍ የቦንድ ሽያጭ ዛሬ ተጀምሯል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በወቅቱ እንዳሉት፤ የግድቡ ግንባታ ዜጎች ባደረጉት አስተዋጽኦ ወደ ፍጻሜ እየደረሰ ያለ የትውልዱ አሻራ ነው።
ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎችም ዓለም አቀፍ አንድምታዎች እንዳሉትም አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ግድቡን በራስ አቅም በመገንባት ውስጣዊ አንድነታችንን ያጠናከርንበት ውጤት ያገኘንበት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በዚህ ግድብ ላይ አስተዋጽኦ የምናደርግ ሁሉ ታሪክ እየሰራን ስለሆነ ደስ ሊለንና ኩራት ሊሰማን ይገባል በማለት ገልጸው፤ ግድቡ ለረጅም ዘመናት አገልግሎት እንዲሰጥ ተፋሰስ አካባቢዎች የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ይህም ግድቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በታቀደው ዓመት ልክ አገልግሎት እንዲሰጥ ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
ግድቡ ሌሎች ተጨማሪ ግድቦችን ለመገንባት አቅምና የይቻላል መንፈስ መፍጠሩን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በአንድነትና በትብብር መንፈስ ግንባታውን ከፍጻሜ ማድረስ አለብን ብለዋል።
በ8100፣ በቦንድ ግዢ፣ በገንዝብና በሌሎች መልኮች የሚደረገው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው የኢትዮጵያውያን የአብሮነትና ጥንካሬ ማሳያ በሆነው የግድቡ ግንባታ የክልሉ ሕዝብ የሚያደርገውን ተሳትፎ እንደሚያጠናክር አረጋግጠዋል።
የክልሉ ሕዝብ በግድቡ ግንባታ በተፈጠረው ሥራና እየተፈጠሩ በሚገኙት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተጠቃሚ በመሆን ላይ እንደሚገኝም ገልጸው፤ ህዝቡ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን በሁሉም ዘርፎች እንዲያጠናክር ጠይቀዋል፡፡
በየደረጃው ያሉ አመራሮችና ባለሙያዎች ለግድቡ የሚደረግ ድጋፍ ከጽህፈት ቤቱ ጋር በመተባበር በግንባር ቀደምነት እንዲያስፈጽሙም አሳስበዋል፡፡
በዝግጅቱ ከተሳተፉት የአሶሳ ነዋሪዎች መካከል አቶ ሃብተማርያም ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት በመጀመሩ የድካማችንን ፍሬ በተግባር ተቋድሰናል ብለዋል፡፡
''በራሳችን አቅም መልማት እንደምንችል ያሳየንን ፕሮጀክታችንን እስከ ፍጻሜው ገንዘብን ጨምሮ ተግባራዊ ድጋፍ ማድረጋችንን እንቀጥላለን'' ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በአሶሳ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ የተጀመረው ሃገር አቀፍ የቦንድ ሽያጭ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ተገልጿል፡፡