የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ግዙፍና ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና ሊጫወት ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ግዙፍና ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና ሊጫወት ይገባል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) መጋቢት 16/2015 የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ግዙፍና ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና ሊጫወት ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ በተለያዩ መስኮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች አስመርቋል።
ተመራቂዎቹ በምህንድስናና ጤና ሳይንስ መስኮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።
በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፣ ከፍተኛ መኮንኖችና የተለያዩ አገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
የኢፌድሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደተናገሩት ባለፉት ዓመታት ትልልቅ አገራዊ ግዳጆችን በብቃት የተወጣ ሰራዊት ተገንብቷል።
አሁንም ሰራዊቱ ማንኛውም ግዳጆችን በአኩሪ ደረጃ መፈጸም የሚያስችል ዝግጁነት ደረጃ ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
ሰራዊቱ አሁን ለደረሰበት ደረጃ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ሚና ትልቅ መሆኑን አስታውሰው በቀጣይም ይሄው አስተዋጽዖ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።
በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ዘመናዊና ግዙፍ ሰራዊት የመገንባት ግብ ተይዞ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው ግቡ እንዲሳካ ዩኒቨርስቲው የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባውም ነው ያሳሰቡት።
በአሁኑ ወቅት አገሪቷ በርካታ የሰለጠነ ሰራዊት ትፈልጋለች ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ በዚህ ረገድ ዩኒቨርስቲው ብዙ መስራት እንደሚጠበቅበትም አስገንዝበዋል።
ሰራዊቱ በዕውቀትና በቴክኖሎጂ በራስ አቅም እንዲገነባ በማድረግ በኩል የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባውም ነው ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ አጽንኦት የሰጡት።
የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ረጋሳ እንደገለጹት ዩኒቨርስቲው ተልዕኳቸውን በብቃት የሚወጡ ወታደሮችን በማፍራት ላይ ይገኛል።
የሰራዊቱን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚረዱ ጥናትና ምርምሮች ከማስተማር ጎን ለጎን ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑንም አንስተዋል።
የመከላከያ ሠራዊት የሰለጠነ የሰው ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በምህንድስና፣ በጤና፣ በኃብት አስተዳደር መስኮች ከዲፕሎማ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ገልጸው በምህንድስና የትምህርት መስክ በሦስተኛ ዲግሪ ደረጃ ማስተማር መጀመሩን አብራርተዋል።
ዩኒቨርሰቲው ወላጆቻቸው በግዳጅ የተሰዉ የሰራዊቱ አባላት ልጆች በነጻ የትምህርት ዕድል እየሰጠ ነው ያሉት ብርጋዴር ጀነራል ከበደ ለፌደራል ፖሊስና አካበቢው ነዋሪዎችም የሥልጠና ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ባሻገርም ዩኒቨርስቲው ከጎረቤት አገራት ለሚመጡ ሰልጣኞች ተገቢው እውቀት እንዲጨብጡ በማድረግ ቀጣናዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ተፈላጊውን ሙያተኛ ለማውጣት የትምህርት ጥራት ማሻሻያዎች ላይ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው ያገኙትን እውቀት ተግባራዊ በማድረግ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።
በትምህርት ቆይታቸው የላቀ አፈጻጸም ላሳዩ ተመራቂዎች የዋንጫና ሜዳሊያ ሽልማቶች ተበርክቶላቸዋል።