የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን መጻዒ ዘመን የተሻለ ለማድረግ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ መርህ ነው...የህንድ ባለሃብቶች

382

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ)  የመደመር እሳቤ ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን መጻዒ ዘመን የተሻለ ለማድረግ ሁሉም ሊተገብረው የሚገባ መርህ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የሕንድ ባለሃብቶች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የአስደናቂ ታሪክ ባለቤት የሆነችውን ኢትዮጵያ በመምራት ሂደት በተለይ የትውልድ ቀረጻ ላይ ማተኮራቸውን አድንቀዋል።
 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን እና የትውልዱን መጻዒ ብሩህ ተስፋ የሚተልሙ መደመር፣ የመደመር መንገድ እና የመደመር ትውልድ የተሰኙ ሦስት መጻሕፍትን አበርክተዋል።

ሦስቱም መጻሕፍት ማጠንጠኛ 'መደመር' ቢሆንም የመደመር እሳቤው ምንነት፣ ስለትግበራ መንገዱ እና ስለትውልዱ ትግበራ ወሰን በተለያዬ ዐውድ የሚያትቱ ናቸው።

በቅርቡ የተመረቀው 'የመደመር ትውልድ' የተሰኘው ሶስተኛ መፅሓፋቸው የእንግሊዝኛ ቅጂ ለዓለም አቀፉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ እና ለውጭ ባለሃብቶች በታደሙበት የማስተዋወቅ መድረክ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ የሕንድ ባለሃብቶች ፎረም ምክትል ሰብሳቢ ራጂቭ ሻርማ እንዳሉት፤ መፅሐፉ የመደመር ትውልድ ከትናንት እንዲማርና የራሱን አቅሙን አሰባስቦ የተሻለች ሀገር እንዲገነባ መንገድ ያሳያል።

የመደመር እሳቤ ዓለም አቀፋዊ መርሆን የሚያስተጋባ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተቀረው ዓለም የሚበጅ መሆኑንም እንዲሁ።

አፍሪካውያን ከቀደመ ታሪካቸው እንዲማሩ፣ እርስ በርስ እንዲተዋወቁ ብሎም ወደ ፊት ጠንካራ አህጉር መገንባት የሚያስችል አቅማቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ መንገድ የሚጠቁም መሆኑንም ተናግረዋል። 


 

የህንድ የቢዝነስ ፎረም አባል ካውሸል ሼድ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ጥንታዊትና አኩሪ ታሪክ ያላት እና መልከ ብዙ ውጣ ውረዶችን ያሳለፈች ሀገር መሆኗን አውስተዋል።

የዘመኑ ትውልድም ከትናንት ታሪክ ቁም ነገሮችን ቀስሞ፤ በመደመር እሳቤ የተሻለ ነገን መገንባት እንደሚችል መመላከቱን ጠቁመዋል።

ከቅደመ አያቶቻቸው ጀምሮ ቤተሰቦቻቸው ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖራቸውን የሚናገሩት ሕንዳዊ ባለሀብት ሀርሺ ኮታሪ፤ መደመር በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ የተለያዩ ሀብቶችን አሰባስቦ በመጠቀም ሀገርን መለወጥ እንደሚቻል የሚያሳይ እሳቤ ነው ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲሱ የመደመር ትውልድ መፅሐፋቸው የትናንት፣ የዛሬ እና የነገ ትውልዶች   ዕውቀት፣ ጉልበት፣ ጊዜና ጥበባቸውን ለጋራ ዓላማ ማዋል እንደሚገባቸው አሳይተዋል ነው ያሉት።

የነገ ትውልድ ጥበብና አቅሙን አዳብሮ ሀገሩን በዓለም ላይ ከፍ ያለች ኢትዮጵያን ዕውን እንዲያደርግ መንገድ ጠቁሟል ብለዋል።

የመደመር ትውልድ የዓለም አንድ አካል በመሆኑ ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም ጋር ያላትን ትስስር እንዲያጎለብትና ሀብቱን አሟጦ እንዲጠቀም የአደራ መልዕክት ያስተላለፈ መፅሐፍ ነውም ብለዋል።

ሌላኛው ባለሃብት ባህበሽ ኢንዳሪያ ብዝሃነት በሞላባት ዓለም ውስጥ ብዝሃ ጸጋን በአግባቡ ተጠቅሞ አካታች ዕድገትና ስልጣኔን ለማረጋገጥ የመደመር እሳቤ የወቅቱ መፍትሔ አመላካች መሆኑን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ'መደመር ትውልድ' መፅሐፋቸው ትውልዱ ለጋራ መዳረሻውን ውስጣዊ አቅሙን ይፈትሽ ዘንድ የዕውቀት ብልጭታ እንደሰጡ ጠቁመዋል።

ባለሃብቶቹ አፍሪካዊያን ሀገር በቀል ጥበብ እንዳላቸው ጠቅሰው፤ የሀገራት መሪዎች ትውልድ ግንባታ በመጻፍና ሰርቶ በማሳየት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን አርዓያ ሊከተሉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የመደመር እሳቤ በራስ መተማመንና የማሳካት አቅም ያዳበረ ትውልድ በመገንባት የኢትዮጵያን፣ የአፍሪካ እና የዓለምን በርካታ ችግሮች መቅረፍ እንደሚቻልም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ መሪነት ሚናዋ፣ ለመካከለኛው ምስራቅ ስትራቴጂክ ስፍራነቷ እንዲሁም በዓለም ላይ ፈጣን ዕድገት ላይ ከሚገኙ ሀገራት ተራ የተሰለፈች ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ዓለም ያለው የመደመር ትውልድ ይበልጥ የበለጸገች፣ የታፈረች እና የተከበረች ኢትዮጵያን የመገንባት ማድረግ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል። 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም