መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በድጋሜ ተመርጡ

297

 አዲስ አበባ  (ኢዜአ) መጋቢት 16/2015  የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ላለፉት ሶስት ዓመታት የመሩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው በድጋሜ ተመርጡ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤውን አካሂዷል።

በጉባኤው ቀጣይ ሶስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበርን የሚመሩ የዳይሬክተሮች የቦርድ አባላት ምርጫ አካሂዷል ።

በዚህም ከ15 ክለቦች እጩዎችን የቀረቡ ሲሆን ሰባቱ በአባልነት ተመርጠዋል።

ሊጉን ላለፉት ሶስት ዓመታት የመሩት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ፤ ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው ተመርጠዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ጌቱ ደጉ ምክትል ሰብሳቢ ሆነው ሲመረጡ ንዋይ በየነ፣ መንግስቱ መሀሩ፣ አብዮት ብርሃኑ፣ አሰፋ ሆሲሶ እና ልዑል ፍቃዱ የቦርድ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

በቀጣይ ሶስት ዓመት ፕሪሚየር ሊጉ የተሻለ ገቢ እንዲያመነጭና ምስራቅ አፍሪካ ላይ ጥሩ ሊግ እንዲሆን የሚሰሩ መሆኑን የቦርዱ ሰብሳቢ ሆነው በድጋሜ የተመርጡት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ገልጸዋል።

ከሱፐር ስፖርት ጋር ውል በመግባት የቀጥታ ስርጭት ገቢ የማመንጨት ጅምሮች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው ለሊጉ እድገት የሚያግዙ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ይሰራል ብለዋል።

የእግር ኳስ ሜዳ ችግር ለዘርፉ እድገት ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሁሉንም ትኩረት እንደሚሻ ተናግረዋል።

የእግር ኳስ ሜዳዎች መገንባት የፌደራል መንግስትና የክልሎች ሃላፊነት መሆኑን ጠቅሰው በጅምር ላይ ያሉ የስታዲሞች ግንባታ እንዲጠናቀቅ መስራት ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ፤ አክሲዮን ማህበሩ በተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይም የፕሪሚየር ሊጉን የገቢ ምንጭና አቅሙን ማጠናከር ላይ በርብርብ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም