በሐረር ከተማ ዘንድሮ ከ227 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ በርካታ የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል--የከተማው አስተዳደር

139

ሐረር መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ)፦በሐረር ከተማ በበጀት ዓመቱ እስከ አሁን በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከ227 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን  የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።

የማዘጋጃ ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢስማኢል ዮስፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ባለሃብቶችንና ሌሎችንም  የከተማ ነዋሪዎችን በማሳተፍና ንቅናቄ በመፍጠር የተለያዩ  የልማት ሥራዎች ተከናውነዋል።

በከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማዳረስ ተጨማሪ 16 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ዳር የመብራት መስመር መዘርጋቱን ጠቅሰዋል።


እንዲሁም 3 ነጥብ 96 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፤ 10ሺህ 611 ካሬ ሜትር አረንጓዴ ስፍራዎችን የማስዋብ ሥራ መከናወኑንም አስረድተዋል።


የመሰረተ ልማት ሥራዎቹ ነዋሪው ሲያነሳ የነበረውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ከማገዛቸውም በላይ  ከተማዋን ውብ፣ ጽዱና ነፋሻማ እንድትሆን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ 


በተለይም በአለም ቅርስነት የተመዘገበው ጀጎል ግንብ ዙሪያ የተገነቡት የአረንጓዴ ስፍራዎች ቅርሱ በዘላቂነት እንዲጠበቅ ከማመቻቸታቸውም ባለፈ የቱሪስቱን ቆይታ በማራዘም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማጠናከር አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።


በከተማዋ ከደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ጋር በተያያዘ ያሉትን ችግሮች ለማቃለልና በዘርፉ ለዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ረገድም አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።


''በአሁኑ ወቅትም የ100 ቀን እቅድ ተዘጋጅቶ የህዝቡን ተሳትፎ በማጠናከር በከተማው ውስጥ የተለያዩ  የልማት ሥራዎች  እየተከናወኑ ይገኛሉ'' ሲሉ ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል። 


በከተማዋ የሺእመቤት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሰይፉ ከበደ በሰጡት አስተያየት ፤ቀደም ሲል በትምህርት ቤቱ የእግረኛ መንገድና የመንገድ መብራት ባለመኖሩ በተማሪዎች ላይ የተለያዩ ጉዳት ይደርስ እንደነበር አስታውሰዋል።


የመሰረተ ልማት ሥራው በአካባቢው የነበሩ ችግሮችን ከማቃለሉም ባሻገር አካባቢው ነፋሻማና የመዝናኛ ስፍራ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


በትምህርት ቤታቸው አካባቢ የመንገድ መብራትና የእግረኛ መንገድ ባለመኖሩ ተማሪዎችን ብቻ ሳይሆን አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ይቸገሩ እንደነበር የተናገረው ደግሞ ተማሪ ፋሲል ወንድሙ ነው።


ዘንድሮ የመሰረተ ልማቱ ሥራ በመከናወኑ የነበረው ችግር መቃለሉን ገልጿል።


ቀደም ሲል በአካባቢው የመሰረተ ልማት ባለመሟላቱ ቅሬታ አድሮብን ቆይቷል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ትሻገር ፋንታ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው በተከናወኑት የልማት ሥራዎች ነዋሪው ሁሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል። 


የመሰረተ ልማቶቹ ለአካባቢው ውበትና ለነዋሪው መዝናኛ ሆነዋል ያሉት ወይዘሮ ትሻገር፤ ለህዝቡ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለሰጠው ለክልሉ መንግስት ምስጋና አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም