ተመራቂዎች ያገኙትን እውቀት ለአገር ግንባታ ማዋል ይኖርባቸዋል - የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ

129

ወልዲያ  መጋቢት 16 /2015 (ኢዜአ)፡-  ተመራቂዎች ባገኙት እውቀት ሕዝብን በታማኝነት ማገልገልና በአገር ግንባታ ስራው የድርሻቸውን እንዲወጡ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ አሳሰቡ። 

ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ትምህርት መስኮች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ  ያሰለጠናቸውን 593 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።


 

በጤና ሳይንስ ኮሌጁ ካስመረቃቸው 481 ተማሪዎች በተጨማሪ በሌሎች የትምህርት መስኮች በድህረ ምረቃ 112 ሰልጣኞችን ያስመረቀ ሲሆን ከቅዱስ ላሊበላ ቅርስና ጥናት ግቢ 25 ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ዛሬ በድህረ ምረቃ መርሐግብር ያስመረቀበት የሚጠቀስ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አበበ ግርማ በድህነት ውስጥ ያለን ሕብረተሰብ መታደግ የምሁራን ቀዳሚ ድርሻችን ነው ብለዋል።

ተመራቂዎች ሕዝብና አገር የጣለባቸውን አደራ በሚሰማሩበት መስክ ሁሉ በቅንነትና በታማኝነት በማገልገል መወጣት እንዳለባቸው  አመልክተዋል።

ያገኙትን እውቀት ለአገር ግንባታ በማዋል የበኩላቸው ድርሻ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የወልዲያ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ዶክተር ዳዊት መለስ በበኩላቸው፤ "የዛሬ ተመራቂዎች ችግር ሳይበግራችሁ በፅናት ለዛሬ ምረቃ በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ" ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው ተመራቂዎች በበኩላቸው በተመረቁበት ሙያ ኢትዮጵያን ለማገልገልና ትውልድን የሚጠቅም ስራ ለማከናወን በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በትምህርታቸው ብልጫ ውጤት ላመጡ ተመራቂዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። 

ወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የትምህርት መርሃ ግብሮች ከዘጠኝ ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም