በዶሮ እርባታ ውስጥ የሚያጋጥመውን በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው - የግብርና ሚኒስቴር

214

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ)፦  በዶሮ እርባታ ውስጥ የሚያጋጥመውን በሽታን አስቀድሞ መከላከል ላይ ያተኮረ አካሄድ  እየተከተለ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የስነ-ሕይወት ደህንነቱ የተጠበቀ ምርታማ የዶሮ ሃብት ልማት ላይ ያተኮረ የዶሮ ጤና አጠባበቅና እርባታ ስልጠና በቢሾፍቱና በደብረ ብርሃን ከተማ በይፋ አስጀምሯል።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብቷ ቀዳሚ ናት ብትባልም ከዘርፉ የምታገኘው ጥቅም ዝቅተኛ መሆኑን ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ውብሸት ዘውዴ ይገልጻሉ።

አገሪቱ ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ከፍ ለማድረግ የሌማት ትሩፋት መርሐግብር ይፋ መሆኑን ገልጸው መርሐግብሩ ከውጭ የሚገባውን እንስሳት ተዋጽኦ በአገር ውስጥ ምርት በመተካትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ዓላማ ማድረጉን ተናግረዋል። 

በሌማት ትሩፋት ከተያዙ የትኩረት መስኮች አንዱ ደግሞ የዶሮ እርባታ መሆኑን ጠቅሰው ጥራትና ምርታማነትን በመጨመር፤ ዶሮና እንቁላል ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ የነበረው የዶሮ እርባታ ዘዴና ሂደት ደህንነቱ ያልተጠበቀ በመሆኑ የዶሮ በሽታ ከተከሰተ በቀላሉ ለከፋ ጉዳት እንደሚዳርግ ነው ዶክተር ውብሸት ያብራሩት።

በዚህም ሚኒስቴሩ የዶሮ ልማትን ከማስፋፋት ባሻገር የእርባታ ስርዓቱ የስነ-ሕይወት ደህንነቱን እንዲጠብቅ ለአርቢዎች የዶሮ ጤና አጠባበቅና እርባታ ስልጠና መርሐግብር መጀመሩን ጠቁመዋል።


 

ስልጠናው በዶሮ ልማት የሚታወቁ በኦሮሚያ 12 ወረዳዎችና በአማራ 9 ወረዳዎች መጀመሩን ገልጸው በቀጣይነት ሰልጣኞች ሌሎች አርሶ አደሮችን እያሰለጠኑ የሚሄዱበት ስርዓት ይዘረጋል ነው ያሉት።

የግብርና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ዴስክ ኃላፊ ዶክተር ካሳው አምሳሉ በበኩላቸው የዶሮ እርባታ በተለይ በሽታን በመከላከል ረገድ ጥንቃቄ የሚጠይቅ በመሆኑ የአደጋ ስጋት ትንተናን መሰረት በማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጫጩት ለማስፈልፈል ከውጭ የሚገባው የለማ እንቁላል በተመለከተ በኤርፖርት ጭምር ምርመራ በማድረግ ጤንነቱ ከተረጋገጠ ብቻ ወደ አገር ቤት በማስገባት፤ ጤናማ ያልሆነው እንደሚወገድ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የመንግስት ትኩረት ለአርቢዎች በእውቀትና ክህሎት ተደግፈው እንዲያረቡ በማስቻል የዶሮ ምርታማነትን መጨመርና ከዘርፉ ተገቢውን ውጤት ማግኘት ነው ብለዋል።

በዚህም በሽታዎች እንዳይከሰቱ መከላከል እንዲሁም ከተከሰቱ በቀላሉ እንዳይሰራጩ የሚያደርግ ስርዓት መከተል ላይ ትኩረት መደረጉንም ነው ዶክተር ካሳው ያመለከቱት።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም