የሀገርና የህዝብን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት ከሁሉም የእምነት ተቋማት ይጠበቃል--የሰላም ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የሀገርና የህዝብን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት ከሁሉም የእምነት ተቋማት ይጠበቃል--የሰላም ሚኒስቴር

ባህር ዳር መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ) የሀገርና የህዝብን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮችን በውይይት መፍታት ከሁሉም የእምነት ተቋማት መሪዎችና የእምነቱ ተከታዮች እንደሚጠበቅ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ የሚያጋጥሙ ችግሮች በሰከነ አግባብ በውይይት እንዲፈቱ ከተቋማት ጋር ተቀራርቦ መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
የሰላም ሚኒስቴር ከአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር "የሃይማኖቶች አስተምህሮ ለሰላም" በሚል መሪ ሀሳብ ያዘጋጀው ክልል አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በባህር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
የሰላም ሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር እሸቱ ደሴ በእዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በሃይማኖቶች መካከል ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህል እንዲዳብር ሚኒስቴሩ ከተቋማቱ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።
የሚፈጠሩ ችግሮችን በወቅቱ በውይይት በመፍታት ነባሩን የአብሮነትና የመቻቻል ባህልና እሴቶችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልፀዋል።
የሰላም ኮንፈረንሱ ሃይማኖቶች ተቀራርበው በመስራት ችግሮች ሲፈጠሩ ስር ሳይሰዱ በንግግርና በውይይት እንዲፈቱ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አስረድተዋል።
"በተለያየ መልኩ የሀገርና የህዝብን ሰላም ሊያደፈርሱ የሚችሉ ችግሮች ሲከሰቱ በውይይት መፍታት ከሁሉም የእምነት ተቋማት መሪዎችና ተከታዮች ይጠበቃል" ሲሉም አማካሪው ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ ከዚህ በፊት ከተቋማት ጋር ተቀራርቦ በመስራት የተለያዩ ችግሮችን መፍታቱን ያስታወሱት አምባሳደር እሸቱ፤ "በቀጣይም የሚገጥሙ ችግሮችን በሰከነ አግባብ በውይይት ለመፍታት በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።
"ሰላም ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይ የእምነቱ ተከታዮችን ሰብዕና ለመገንባት የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።
ተቋማቱ ተከታዮቻቸው ከጥላቻ ራሳቸውን እንዲያርቁ ስለሰላም ጠቀሜታ አዘውትረው ሊያስተምሩ እንደሚገባም አምባሳደር እሸቱ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የሃይማኖትና እምነት ተቋማት ዳይሬክተር አቶ አለኽኝ መለሰ በበኩላቸው፣ የእምነት ተቋማት ለሰላም ግንባታ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ቢሮው በክልል ከሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ችግሮች እንዳይፈጠሩ የሚያስችሉ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ለአንድ ቀን እየተካሄደ ባለው መድረክ ከሰላም ሚኒስቴርና ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የፀጥታ አካላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።