መንግስት የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ

442


አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015( ኢዜአ)፦መንግስት የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ ከጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ የልማት ጉዳዮች ተወያይተዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች የሰላም፣ የልማትና አስተዳደራዊ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።


 


ነዋሪዎቹ በጥያቄዎቻቸው በዞኑ የውሃ፣ የመንገድ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማት ተደራሽነት ችግር መኖሩን ተናግረዋል።

ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና መፍጠሩን ገልጸዋል።

በመሆኑም የጉራጌ ዞን ራሱን ችሎ በክልልነት በመደራጀት የልማት ጥያቄዎቹን ለመፍታት ያቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ይገባል የሚል ጥያቄ ተነስቷል።

ነገር ግን የክልልነት ጥያቄን እንደሽፋን በመውሰድ በዞኑ አብረው በጋራ የኖሩ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚሰሩ አካላት መኖራቸውን የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፣ እነዚህ አካላት ተለይተው ለህግ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል።


 


ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ፤ በምላሻቸው በሁሉም አካባቢዎች በርካታ የመልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ መንግስት ያሉትን አቅሞች በማሰባሰብ ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


ከዚህ አኳያ መንግስት የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ላነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።


ከህዝቡ ለተነሱት የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ ባለሃብቶችም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።


አስተዳደራዊ አደረጃጀት ለጥያቄዎች ሁሉ መልስ መስጫ መፍትሔ አለመሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች ከአጎራባች ዞኖች ጋር ያላቸውን አብሮነት በማጠናከር በጋራ ለመልማት መስራት አለባቸው ብለዋል።


የሚነሱ ጥያቄዎችን በሰለጠነና በሰከነ አግባብ መፍታት እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም