በኢትዮጵያ ከስደት የተመለሱ ዜጎችን ለማቋቋም የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት

207

አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ)፦  ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት(አይኦኤም) በኢትዮጵያ ከተለያዩ የዓለም አገራት ከስደት የተመለሱ ዜጎች ለማቋቋም የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ተግባራዊ እያደረገች ባለው ዜጋ ተኮር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በተለያዩ የዓለም አገራት በችግር ውስጥ የነበሩ ዜጎች ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው። 

በተለይም የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በሳዑዲ አረቢያ፣ የመን፣ ቤሩትና ሌሎች በመካከለኛው ምስራቅ አገራት የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ተደርጓል። 


 

በተመሳሳይ በአፍሪካ አገራትም በሕገ-ወጥ ስደት በእስርና በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የነበሩ ዜጎች ከአገራቱ ጋር በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ መግባባቶች መመለሳቸው ይታወሳል።

መንግስትም በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ከስደት ተመላሽ ዜጎች መልሶ ለማቋቋምና በአገራቸው ሰርተው እንዲለወጡ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። 

የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅትም ይህንን የመንግስት ጥረት ለማገዝ በተለይም ስደተኞቹ መልሰው እንዲቋቋሙ የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው በድርጅቱ የምስራቅና የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ዶክተር ሞሃመድ አብዲከር የሚናገሩት። 

ድርጅቱ የስደት ተመላሾች በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በአጭር ጊዜ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችላቸውን ከስነ-ልቦናና የማማከር አገልግሎት አንስቶ የተለያዩ የስራ ፈጠራና የንግድ ሥራ ክህሎት ላይ ትኩረት  ያደረጉ ስልጠናዎችን በተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች እያቀረበ ነው ብለዋል።    

የአቅም ግንባታ ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ኢትዮጵያ ከፍልሰት ጋር ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች በፖሊሲ ደረጃ ትኩረት ሰጥታ ለማከናወን ያላት ቁርጠኝነት በአድናቆት እንደሚመለከቱት ገልጸዋል።

ድርጅቱም ፍልሰትንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ ትኩረት አድርገው ከሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር እንደሚሰራ ነው ዶክተር ሞሃመድ የተናገሩት። 

በሌላ በኩል ከፍተኛ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር የሚስተዋልበት የአፍሪካ ቀንድ ሕጋዊና ደህንነቱ የተጠበቀ የሰዎች እንቅስቃሴን ለመዘርጋት ድርጅቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ከመንግሥት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል። 

በተለይም ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከርና የቁጥጥር ስርዓቱን በማጎልበት ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ ግብረ ኃይል የሚከናወኑ ተግባራትን ለማጠናከር ድጋፉ ይቀጥላል ነው ያሉት። 

ኢትዮጵያውያን በመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓና ሌሎች የዓለም አገራት ሙያን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን ሄደው እንዲሰሩም ከመንግሥት ጋር አማራጮችን እያፈላለገ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም