የመከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት የምታስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአገር ውስጥ ለመተካት የጀመረውን ጥረት ማጠናከር አለበት -የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም  ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

373


አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርስቲ ኢትዮጵያ ዘመናዊ ሰራዊት ለመገንባት ከውጭ የምታስገባቸውን ቴክኖሎጂዎች በአገር ውስጥ ለመተካት የጀመረው ጥረት በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሳሰቡ።


ዩኒቨርሲቲው በምህንድስናና ጤና ሳይንስ የትምህርት መርሐ-ግብሮች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ተማሪዎችን  አስመርቋል።


በምርቃት መርሐ-ግበሩ ላይ የኢፌዴሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም  ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ፣ከፍተኛ  መኮንኖችና የተለያዩ  አገራት ወታደራዊ  አታሼዎች ተገኝተዋል ።


የአገር መከላከያ ሰራዊት የሚገጥሙ ፈተናዎችን በብቃት እያለፈ እንደሚገኝና ለዚህም እንደ የኢትዮጵያ  መከላከያ ዩኒቨርስቲ አይነት የትምህርት ተቋማት ትልቅ ሚና  መጫወታቸውን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ገልጸዋል።


ዘመኑ የቴክኖሎጂ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ቴክኖሎጂዎችን ማፍለቅ ላይ ርብርብ ማድረግ እንዳለበት ተናግረዋል።


“መከላከያን የማዘመኑ ሂደት ቴክኖሎጂን ይፈልጋል ይህን ደግሞ ከውጭ በማስገባት ብቻ አይቀጥልም” ያሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹሙ ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባው ቴክኖሎጂ መተካት ላይ የጀመረውን ጥረት እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።


የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዴር ጄኔራል ከበደ ረጋሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከ75 በላይ መደበኛ መርሐግብሮች እንዳሉት ገልጸዋል።


በነዚህ መርሐ-ግብሮች ተልዕኮውን በብቃት የሚወጣ ሰራዊት በማፍራት ላይ እንደሚገኝና በጥናትና  በምርምር ዘርፍም ዘመናዊ  ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ዘመናዊ ሰራዊት  እንዲገነባ እየሰራ ነው ብለዋል። 


ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት በሶስተኛ ዲግሪ መርሐግብር መስጠት መጀመሩን ገልጸው በዩኒቨርሲቲው የሚሰጠውን ትምህርት ጥራት ለማሻሻል የስርዓተ ትምህርት ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን ነው ብርጋዴር ጀኔራሉ ያብራሩት።


በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አኳያ በግዳጅ ምክንያት ሕይወታቸውን ላጡ  የአገር መከላከያ ሰራዊት አባላት  ልጆች  ነጻ የትምህርት  ዕድል እየሰጠ መሆኑን  ገልጸዋል።


በምርቃት መርሐ-ግብሩ ላይ የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች ሽልማት ተበርክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም