አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተጀመረ
አሶሳ መጋቢት 16/2015 (ኢዜአ):-የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበት 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ አገር አቀፍ የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ሳምንት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።
የቦንድ ሳምንቱ የግድቡ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የግድቡን 12ኛ ዓመት አስመልክቶ ካዘጋጃቸው የገቢ ማሰባሰቢያ እና ሌሎች ሁነቶች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃገር አቀፍ ህዝባዊ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በዚህ ወቅት “የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እንደ አድዋ ድል ከፍተኛ የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት ነው” ብለዋል።
ይህም ኢትዮጵያን ከውጪ ብድርና እርዳታ ተላቃ ነጻ ኢኮኖሚ እንድትጎናጸፍ ለማድረግ ለምታደርገው ጥረት ተጨባጭ ተስፋ የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህን ተስፋ በማስቀጠል አንድነትን በማጠናከር በግድቡ ላይ የቀጠለውን የውጪ ጫና ማስቆም እንደሚገባም ተናግረዋል።
“ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ መንግስት እና ሕዝብ ያሳዩት ዓለምን ያስደመመ ቅንጅታዊ አካሄድ ዛሬም ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ማዋል ይገባል “ነው ያሉት ዶክተር አረጋዊ።
ሕብረተሰቡ በአባይ ተፋሰስ የሚካሄዱ የአካባቢ የጥበቃ ስራዎች ላይ በመሳተፍ እንዲሁም ለግድቡ በገንዘብና በቦንድ ግዢ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ለአንድ ወር ይቆያል።
የቤኑሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግራኝ ጉዳታ በበኩላቸው ከ2013 ዓም ጀምሮ ከክልሉ ከ100 ሚሊየን ብር ለግድቡ ገቢ ተሰብስቧል ብለዋል::
ለግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል::
በመርሃ ግብሩ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በየደረጃው የሚገኙ የስራ ሃላፊዎች እና ነዋሪዎች እየተሳተፉ ነው::
አገር አቀፍ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቦንድ ሳምንት ለአንድ ወር የሚቆይ ሲሆን 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱንም ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።