የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገለጸ

594


አዲስ አበባ መጋቢት 16/2015(ኢዜአ)፦ የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ለኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ትግበራ እያደረገ ያለውን ድጋፍ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ፒ.ኤች.ዲ.) ከቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት ዋና ሊቀመንበር ሰር ቶኒ ብሌር ጋር በጽህፈት ቤታቸው ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለው ትብብርና በቀጣይ ለመስራት ባቀዷቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ማህበራዊ ትስስር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የቶኒ ብሌር ኢንስቲትዩት የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 (ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን) ስትራቴጂ ከዝግጅት ወቅት አንስቶ እስከ ማስፈጸም ሂደት በቴክኒክ(ባለሙያ)፣በኢ-ሰርቪስ ትግበራ ላይ ጥናት በማድረግ፣የማስፈጸም አቅም እንዲሁም የአደረጃጀትና የስራ ሂደትን ለማሻሻል የሚያስችል ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል። 

ኢንስቲትዩቱ ከዲጂታል መሰረተ ልማት አኳያ በዳታ ሴንተር፣በኢንተርኔት ተደራሽነት፣ በክላውድና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ላይ በቀጣይ ሊያደርገው በሚችለው ድጋፍ ውይይት መደረጉ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮዳሄ ዘሚካኤል ለሰር ቶኒ ብሌር የዲጂታል መታወቂያን አገልግሎቶች አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዳይሬክተሩ ኢንስቲትዩቱ ለአገልግሎቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ከመሰረተ ልማት ጋር ያሉ ተግዳሮቶች ላይም ገለጻ አድርገዋል።   

የ69 ዓመቱ የእንግሊዝ የቀድሞ ፖለቲከኛ አገሪቷን ከእ.አ.አ 1997 እስከ 2007 በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም