ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል -የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራው ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስካሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርጓል -የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት
አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015(ኢዜአ)፡- ዳያስፖራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ እንስቶ እስካሁን ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።
በኢትዮጵያውያን ገንዘብና ጉልበት ብቻ እየተገነባ የሚገኘው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በመጋቢት ወር 2003 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ የሚታወስ ነው፡፡
በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሶስት ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት እንዳሉ ይገለጻል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወንደወሰን ግርማ ለኢዜአ እንገለጹት፤ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትወልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ስኬታማነት በጉልበት በገንዘብና በሀሳብ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል።
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሉ 12 ዓመታት ውስጥ ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ከገንዘብ ድጋፉ ውጪ "የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት የሕዳሴ ግድብን ግንባታ ለማስተጓጎል የሚሞክሩ የውጭ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በአደባባይ በመቃወም እውነታውን ለዓለም በማሳወቅ ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወቱ ነው" ብለዋል፡፡
ሀብት በማሰባሰብ፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲን በማጠናከር፣ እንዲሁም በእውቀትና በቴክኖሎጂ ሽግግር አበርክቶውን እንዲያጠናክር አገልግሎቱ ከዳያስፖራው ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን አቶ ወንድወሰን ተናግረዋል።
ዳያስፖራው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
የሕዳሴ ግድቡ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተጣለበት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የድጋፍ አግባቦች ከ17 ቢሊዮን ብር በላይ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ከታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።