በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በ331 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ ተከናውኗል - የክልሉ ግብርና ቢሮ

728


ሰቆጣ  መጋቢት 15 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በዘንድሮው የበጋ ወራት በ331 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈር እና ውሃ ጥበቃ ስራ መከናወኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።


በክልሉ በበጋው ወቅት የተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎችን እንዲጠብቁ ለአርሶ አደሮች በባለቤትነት የማስረከብ መርሐግብር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ደሃና ወረዳ ሽመላ ቀበሌ ጋውሳ ተፋሰስ ዛሬ ተካሂዷል።


 

የአማራ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አልማዝ ጊዜው የክልሉን የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ ከ14 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የዞንና ቀበሌ ባለሙያዎች የክህሎት ስልጠና መሰጠቱንና 34 ሺህ የሚደርሱ የስራ መሳሪያዎች ለዞኖች መከፋፈላቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በክልሉ 8 ሺህ 548 ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች ለማከናወን ታቅዶ፤ በ8 ሺህ 596 ተፋሰሶች ላይ ስራዎቹ መካሄዳቸውን አመልክተዋል።

በልማቱ በ331 ሺህ ሄክታር ላይ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች መከናወናቸውንና በስራዎቹ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን ጠቁመዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ልማት በዘላቂነት በማከናወን የዜጎችን ሕይወት ለመቀየር የሚያስችሉ ተግባራት ለማከናወን መታሰቡን ነው ዶክተር አልማዝ ያስረዱት።

በቀጣይም የለሙ ተፋሰሶችን በስነ ሕይወታዊ ዘዴዎች የመሸፈንና የኢኮኖሚ ምንጭ የሚሆኑትን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ እንዳሉት፤ በአስተዳደሩ በ277 ተፋሰሶች ውስጥ የሚገኝ 4 ሺህ 927 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ተካሄዷል።


 

በልማቱም ከ82 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውንና በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተካሄዱት ተፋሰሶች የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንዳሳደጉትም ገልጸዋል።

በተለይም  በተራራ ላይ የተሰሩ የጠረጴዛ እርከኖች ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንና ስራዎቹን በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ደሃና ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች  በአካባቢያቸው ባለፉት ዓመታት በወረዳው በተካሄዱት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች በመሳተፍ  የእርሻ መሬታቸውን ለም አፈር በማሳ ውስጥ በማስቀረት ምርታማነታቸውን ማሳደግ መቻላቸውን ገልጸዋል።


 

ዘንድሮ የተካሄዱት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች በአግባቡ እንዲጠበቁና እንዲያገግሙ በየአካባቢያቸው የተፈጥሮ ሃብት ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በዘንድሮው ዓመት በተከናወኑ የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ሶስት ቢሊዮን ብር የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ መደረጉን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያመለክታል'።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም