መንግሥት የገባውን ቃል ገቢራዊ እያደረገ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ገለጸ

280

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015(ኢዜአ)፦ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ቀውስ በዘላቂነት ለመፍታት በፕሪቶሪያ በተደረሰው ሥምምነት መሰረት የፌዴራል መንግሥት የገባውን ቃል እየተገበረ መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት 52ኛ ስብሰባውን በዚህ ሣምንት በስዊዘርላንድ ጄኔቫ አካሂዷል።

በስብሰባው የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት የባለሙያዎች ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ አስመልክቶ ዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የኮሚሽኑ ሰብሳቢ መሐመድ ቻንዴ ኦትማን በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኮሚሽኑ ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ የመጀመሪያውን ሪፖርት ለምክር ቤቱ ካቀረበ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ መሻሻል አሳይቷል።

በደቡብ አፍሪካ ፕሮቶሪያ የተደረሰውን የሰላም ሥምምነት ተከትሎ ጉልህ የሆነ እና እስከ አሁን ድረስ ቀጣይነት ያለው መሻሻል መታየቱን በሪፖርታቸው ይፋ አድርገዋል።

በፌዴራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የተደረሰው የሰላም ሥምምነት ጠቃሚ መሻሻሎች እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።

የፌዴራሉ መንግሥት በፕሪቶሪያ ሥምምነት የገባውን ቃል ተፈፃሚ ማድረጉ በመስኩ ለታየው መሻሻል ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ነው መሀመድ ቻንዴ ኦትማን የገለጹት።

ሥምምነቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት በገባው ቃል መሰረት ወደ ሽግግር የፍትህ ሂደት የሚወስዱ ተከታታይ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን በአዎንታ ገልጸውታል።

በውይይቱ አስተያየቱን የሰጠው የአውሮፓ ኅብረትም በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሓት መካከል ግጭትን የማስወገድ ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በአገሪቱ የታየውን መሻሻል አድንቋል።

የሰላም ስምምነቱና ሥምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉትን እርምጃዎች እንደሚያደንቅ ኅብረቱ ጨምሮ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟላ የሽግግር ፍትህ ማዕቀፍ ቀርፆ ገቢራዊ ለማድረግ ያሳየውን ቁርጠኝነት አወድሶ ኅብረቱ በዚህ ረገድ ልምዱን ለማካፋል ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

በአምባሳደር ሚቸል ቴይለር በውይይቱ የተሳተፈችው አሜሪካም በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ግጭትን የማስቆም ስምምነት ከተፈረሙ በኋላ የታየውን ከፍተኛ መሻሻል በአዎንታ መቀበሏን ገልጻለች።

በተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የአሜሪካ ቋሚ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር ቴይለር እንዳሉት ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ የሽግግር ፍትህን ለመተግበር እያደረገች ያለውን ጥረት የሚበረታታ ነው ብለውታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም