በምስራቅ አፍሪካ የዓሳ ኃብትን ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ርብርብ መደረግ አለበት - ኢጋድ

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015 (ኢዜአ) በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የዓሳ ኃብት በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በቅንጅት መሠራት እንዳለበት የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ገለጸ። 


 

የምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስ ክልል የዓሣ ኃብትን የማልማት አቅምን ለማውጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የኢጋድ ምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በመድረኩ በምስራቅ አፍሪካ የዓሳ ኃብትን በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ተገልጿል።


 

በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የሕንድ ውቅያኖስ ክልል በዓሣ ኃብት ልማት የሚሰራው ኢኮ ፊሽ ቴክኒካል አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ሱኔል ስዌኒሪ በቀጠናው 50 ቢሊየን ዮሮ የሚተመን የዓሳ ኃብት መኖሩን አመላክተዋል።

ያለውን ኃብት በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ የሚገባውን ያህል በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን ገልፀዋል።

በመሆኑም ይህን ኃብት በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማልማት ለአገር ውስጥ ጥቅም እንዲውል እንዲሁም ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማምጣት የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚቻል ተናግረዋል።


 

በኢጋድ የብሉ ኢኮኖሚና ዓሳ ኃብት ከፍተኛ ባለሙያ ዋሴ አንተነህ በበኩላቸው የቀጠናው አገራት በዓሳ ኃብት ከፍተኛ የሆነ እምቅ አቅም እንዳላቸው ገልፀው ይሁን እንጂ ያለውን ያክል ኃብት ጥቅም ላይ አለመዋሉን ተናግረዋል።

በመሆኑም ያለውን የዓሣ ኃብት በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማልማት ለማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ማድረግ የሚያስች አቅምና እድሎች ስለመኖሩ ነው የገለፁት።

በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የዓሳ ኃብት በስፋት ጥቅም ላይ በማዋል ተጨማሪ የምግብ ዋስትና ማረጋገጫ መንገድ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።


 

በውይይት መድረኩ የተገኙት የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ግርማ ሙሉጌታ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓሳ ዘርፍ ያላትን ኃብት በማልማት ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ኃብት ታሳቢ ባደረገ መልኩ በዓሳ ኃብት ልማት ተጠቃሚ ለመሆን የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎችን ከሌላ አካባቢዎች ለማምጣት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም