ቀጥታ፡

ከተለያዩ አገራት የተመለሱ ቅርሶች በብሔራዊ ሙዚየም ለዕይታ ቀረቡ

አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015 (ኢዜአ) ከተለያዩ አገራት የተመለሱ ቅርሶች በብሔራዊ ሙዚየም ለዕይታ መቅረባቸውን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።     

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በተለያየ መንገድ ከአገር የወጡና በተለያየ ጊዜ የተመለሱ ቅርሶችን ከዛሬ ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት በብሔራዊ ሙዚየም ለጎብኚዎች ክፍት አድርጓል።

በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን የብሔራዊ ሙዚየም ዳይሬክተር አቶ ደምረው ዳኜ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአውደ ርዕዩ 20 ታሪካዊ ቅርሶች ለእይታ ቀርበዋል።

ለእይታ የቀረቡት ቅርሶች ባለፉት ሶስት ዓመታት ወደ አገር የተመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከመቅደላ የዛሬ   150 ዓመት በእንግሊዞች ተዘርፈው የተመለሱትን ጨምሮ  ከአሜሪካ፣ ከኔዘርላንድና ከዴንማርክ የተመለሱ ሌሎች ቅርሶችም ለጎብኚዎች ክፍት ሆኗል። 

ባለሥልጣኑ ከቅርስ አስመላሽ ኮሚቴዎች፣ ከኤምባሲዎችና በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ትውልደ አትዮጵያውያን ጋር በተደረገ ጥረት የተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ለዕይታ የቀረቡት ቅርሶች የብራና ጽሁፎች፣ የተለያዩ መስቀሎች፣ አሸንክታብ፣ የዳግማዊ ምኒሊክ ጎራዴ፣ የተለያዩ ዋንጫዎች እና ሌሎች ይገኙበታል ብለዋል።

ከእንግሊዝ አገር የተመለሰው የአፄ ቴዎድሮስ ፀጉር /ቁንዳላ/ ፣ ከ20 ዓመታት በፊት ከኢትዮጵያ ወጥቶ ከኔዘርላንድ የተመለሰው የዘውድ ቅርስ እንዲሁም ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጭምር የተመለሱ ቅርሶች ይገኛሉ።

ቅርሶቹ ለእይታ የቀረቡበት ምክንያት የቅርስ ዝውውር ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር እና ዜጎች የአገር ሀብቶችን በመመልከት ለቅርስ የሚደረገውን ጥበቃ ለማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል።

ቅርሶቹን ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ ህብረተሰቡ ቅርሶችን በመንከባከብ እና ህገ-ወጥ ዝውውር ሲኖር ማጋለጥ አለበት ብለዋል።  

በቀጣይም በፈረንሳይ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን ለማስመለስ በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም