በካፒታል ገበያ ለሚሳተፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት ይጀመራል - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
በካፒታል ገበያ ለሚሳተፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት ይጀመራል - ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015 (ኢዜአ):-የኢንቨስትመንት ባንኮችን ጨምሮ በካፒታል ገበያው ለሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያን ከሶስት ወር በኋላ ፈቃድ መስጠት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡
በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ስርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት የሚያጠናክር የካፒታል ገበያ 'በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013' ተቋቁሟል፡፡
በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ "የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን" መስሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቷል፡፡
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋዮችን በማውጣት የግብይት ስርዓቱን ፍትሃዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ስነ- ምህዳር የመፍጠር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡
ኢንቨስትሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያውን ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት፡፡
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ታዬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ባለስልጣኑ ቦርድና ኃላፊ ተሹሞለት ወደ ስራ በገባባቸው ሶስት ወራት በርካታ ስራዎችን አከናውኗል ብለዋል፡፡
የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ አዲስ እንደመሆኑ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት፣ በገበያው ላይ ለሚሳተፉ የዘርፉ ተዋንያን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር የካፒታል ገበያን ጽንሰ ሀሳብ፣ ጥቅሙንና እንዴት እንደሚሰራ ብሎም በገበያው የሚሳተፉ አካላት እንዴት መግባት እንደሚችሉ ውይይት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በካፒታል ገበያው ለሚሳተፉ ኢንቨስተሮች፣ ደላሎችና ሌሎች የዘርፉ ተዋንያን ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችሉ የተለያዩ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ከሶስት ወራት በኋላ በካፒታል ገበያ የሚያሳትፋቸውን የኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ መስጠት እንጀምራለን ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ስርዓት የውጭ ኢንቨስተሮችን የሚከለክል ሕግ የለም ያሉት ዶክተር ብሩክ፤ ነገር ግን የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ትትን የምናሳካው ግብ የለም ብለዋል፡፡
ባለስልጣኑ ገበያውን በአስተማማኝ ሁኔታ ከመገንባት ባለፈ የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን የማበረታታት ኃላፊነት እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡