በአማራ ክልል የ2015 የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የሽግግርና ርክክብ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የ2015 የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የሽግግርና ርክክብ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው

ሰቆጣ መጋቢት 15/2015(ኢዜአ) የአማራ ክልል የ2015 የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የሽግግርና ርክክብ መርሃ ግብር በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ደሃና ወረዳ እየተካሄደ ነው።
በወረዳው እየተካሄደ ባለው መርሃ ግብር የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለውን ጨምሮ የክልልና የዞኑ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በክልሉ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራው ከጥር 17 ቀን 2015 ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል።
ሽግግርና ርክክቡም በህዝብ ንቅናቄ የለማውን ተፋሰስ በየአቅራቢያው ለሚገኙ ነዋሪዎች በማስረከብ በስነ ህይወታዊ ዘዴ በዘላቂነት እንዲለማ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
"ይህም ተፋሰሱን በመጠበቅና በማልማት በቋሚ አትክልትና ፍራፍሬ፣ በንብ ማነብና መሰል የሥራ ዘርፎች ተደራጅተው ለሚገቡ ወጣቶች የኢኮኖሚ ምንጭ ለመሆንም ያስችላል" ብለዋል።
የብሔረሰብ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በዞኑ ስድስት ወረዳዎች በ119 ቀበሌዎች በህዝብ ተሳትፎ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በ 2 ሺህ 775 ሄክታር መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ሥራ የተሰራ ሲሆን፣ በ2 ሺህ 152 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ ነባር የለሙ ተፋሰሶች ጥገና መደረጉን አስታውቀዋል።
በልማት ሥራው ከ82 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች መሳተፋቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ በሥራዎቹ ከ147 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የጉልበት አስተዋጽኦ ማበርከት ተችሏል ብለዋል።