ኢትዮ-ቴሌኮም በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ ነው-ፍሬህይወት ታምሩ

654

 አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015  (ኢዜአ)  ኢትዮ- ቴሌኮም በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ የመሪነቱን ሚና እየተወጣ መሆኑን የኢትዮ- ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ-ቴሌኮም በአዲስ መልክ ያበለጸገውን ቴሌ ብር "ሱፐር አፕ" የሞባይል መተግበሪያ  ይፋ አድርጓል።

መተግበሪያው ደንበኞች የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማቅለልና በቴክኖሎጂ የታገዘ የንግድ ስራዎችን ለማሳለጥ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በአንድ ጊዜ ፈርጀ ብዙ የዲጂታል ግብይት አገልግሎቶችን እንዲያገኙና ለማንኛውም የግዢ ሂደት እንዲጠቀሙ የሚያስችል መተግበሪያ መሆኑም ተመላክቷል።

ይህ አዲሱ መተግበሪያ አሁን በስራ ላይ ካለው የቴሌብር መተግበሪያ ጋር ተያይዞ የሚታዩ የአፈጻጸም፣ የሴኩሪቲ ሲስተም፣ የስልክ ዳታ የመያዝ አቅም ውስንነትንና ሌሎች የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑም ተነግሯል።

እንዲሁም የማይ- ኢትዮ- ቴል መተግበሪያንና ሌሎች መተግበሪያዎችን በአንድ በማካተት የተቀናጀ፣ ብቁ እንዲሁም አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል ነው ተብሏል።

የኢትዮ -ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኩባንያው አገልግሎቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደገ ይገኛል።

የዲጂታል ኢኮኖሚን እውን የማድረግ ሥራን አጠናክሮ በመቀጠል ኢትዮ-ቴሌኮም በዘርፉ የመሪነት ሚናውን እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።
 
ሀብትን በአግባቡ ለመጠቀም በቴክኖሎጂ መታገዝ ወሳኝ መሆኑን ተናግረው፤ በዛሬው ዕለት ይፋ የሆነውም መተግበሪያ ይህንኑ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል። 

ሌላኛው የስማርት ስልክ አጠቃቀም መሆኑን ገልጸው አሁን ላይ በኔትወርክ ላይ ከተመዘገቡት 81ሚሊየን ቀፎዎች ውስጥ 46 በመቶ የሚሆኑት የስማርት ቀፎዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው መተግበሪያ ቴሌ ብር ሱፐር አፕ ለተለያዩ አገልግሎት የምንጠቀምባቸው አፕሊኬሽኖችን በአንድ መተግበሪያ ላይ ሁሉንም መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ጊዜንና ወጭን በመቆጠብ ረገድ መተግበሪያው ትልቅ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም