ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በጋለሞ-ሞሉድ መንገድ ግንባታ ስምምነት ላይ ደረሱ


አዲስ አበባ መጋቢት 15/2015(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያና ጅቡቲ ሁለቱን ሀገራት የሚያገናኝ የጋለሞ-ሞሉድ ወሳኝ መንገድ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ደረሱ።

በጋለሞ እና ሞሉድ መካከል ያለው የ35 ኪሎ ሜትር መንገድ የተሽከርካሪዎችና የጭነቶች ዝውውር በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲኖር ያስችላል።

ስምምነቱ የተደረሰው በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር አለሙ ስሜ ጅቡቲን በመጎብኘት ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጊሌ ጋር ባደረጉት ስምምነት መሰረት ነው።

ዶክተር አለሙ ስሜ የስምምነቱን አፈጻጸም ለመከታተል በጅቡቲ ይገኛሉ።

በሚኒስትሩ የተመራው ልዑክ በጉብኝቱ ወቅት የመንገዱን ግንባታ ለማፋጠን ከጅቡቲ ወደቦችና ነፃ ዞኖች ባለስልጣን ፕሬዝዳንት አቡበከር ኦማር ሃዲ እና ከልኡካቸው ጋር ተወያይተዋል። 

ስምምነቱ የጋለሞ - ሞሉድ 35 ኪሎ ሜትር መንገድ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚያደርግ ሲሆን ተገቢውን ክፍያም ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን እንዲከፈል ተስማምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን በኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ የሚመራው የልዑካን ቡድን ከመጋቢት 20 እስከ 23 ቀን 2023 ዓ.ም ይፋዊ የስራ ጉብኝት በማድረግ ከጅቡቲ ጉምሩክ ባለስልጣን አቻዎቻቸው ጋር የተለያዩ ጉምሩክ ነክ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።


 

ከሶስት ቀናት ውይይት በኋላ የጉምሩክን ውጤታማነት ለማሻሻል የመፍትሄ ሃሳቦችን በማቅረብ ስምምነት ተፈራርመዋል።

በጋለሞ-ሞሉድ መንገድ ላይ የተደረሰው ስምምነት እና የጉምሩክ ጉዳዮችን አፈታት ጉዳይ ኢትዮጵያና ጅቡቲ ንግድና ትራንስፖርትን ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ባሰፈረው መረጃ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም